አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራና ትግራይ ክልሎች ከጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ 342 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ከጥቅምት 20 ቀን ጀምሮ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ተቋሙ በራሱ አቅም የተለያዩ ድጋፎችን እያሰራጨ ነው፡፡
እስካሁን በሶስት ዙር በተደረገ ድጋፍም በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች 342 ሚሊየን 446 ሺህ 800 ብር የሚያወጣ የሰብዓዊ ድጋፍ መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡
በዚህ መሰረት 150 ሺህ 627 ኩንታል ስንዴ ለ371 ሺህ 291 ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ተደራሽ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለህጻናት እና ነፍሰ ጡር እናቶች የሚውል 14 ሺህ 292 ኩንታል አልሚ ምግብ ወደ አካባቢዎቹ ተልኮ ተሰራጭቷልም ነው ያሉት።
ድጋፉ የተሰራጨው በአክሱም ፣ ሽረ፣ ሽራሮ፣ ራያ ባላ፣ አላማጣ፣ ግዳን እና ኮረም አካባቢዎች መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደበበ÷ለዚህም አጋር አካላትን ያሳተፈ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግና በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋምም ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ