የሀገር ውስጥ ዜና

በርዕሰ መስተዳድር  ይልቃል የተመራ ልዑክ በደቡብ ወሎ ዞን በክላስተር የለማ ስንዴን ጎበኘ

By Shambel Mihret

November 06, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የተመራ ልዑክ በደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ ወረዳ በክላስተር የለማ ስንዴን ጎብኝቷል፡፡

ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ጫና መቆየቷን በጉብኝቱ ወቅት የገለጹት ዶክተር ይልቃል ከፋለ÷ከውጭ  ጫና ነጻ ልንሆን የምንችለው በምግብ ራሳችንን ስንችል ብቻ ነው ብለዋል።

ይህንን ለማረጋገጥ ከአርሶ አደሮች ጋር በመተባበር መስራታችን የሀገራችንን መጥፎ የድህነት ታሪክ እየቀየረ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ከድህነት መውጣት የሚቻለው ዘላቂ ምርትና ምርታማነትን በማረጋገጥ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ለዚህ ደግሞ ሁሉንም የግብርና አማራጭ አሟጦ የመጠቀምና የተሻሻሉ ዘመናዊ አሰራሮችን መተግበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በዚህ አመት በአርሶ አደሩ ትጋትና በመንግስት ጥረት በአንድነት ስንዴን ወደ ውጭ እንልካለን፣ ይህም የሁላችን ድል ነው ብለዋል።

ትጋታችንን ከዚህም በላይ አጠናክረን በመቀጠል እርዳታን የማትቀበል ጠንካራ አገር መመስረት ይገባናል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመሉቀን አበበ