የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል የተጀመረው በርበሬን በኩታ ገጠም የማልማት ሥራ አበረታች መሆኑ ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

November 05, 2022

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተጀመረው በርበሬን በኩታ ገጠም ማሳ የማልማትሥራ የሚደነቅ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ የተመራ ቡድን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጣቁሳ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የበርበሬ ማሳን ጎብኝቷል።

ዶክተር አዱኛ ደበላ ÷ በቀጣይ ተሞክሮውን በሌሎች ክልልሎችም ለማስፋት በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ ያለውን የገበያ ችግር ለመፍታትም የግብይት ሰንሰለት መፈጠሩን በጉብኝት መርሐ-ግብሩ ላይ አብስረዋል፡፡

የጣቁሳ ወረዳ ግብርና ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ጎሼ ወረዳው ቅመማ ቅመም የማምረት ከፍተኛ አቅም እንዳለው ጠቁመው÷ አሁን ላይ 8ሺህ 602 ሄክታር መሬት በቅመማ ቅመም ምርት መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ በበኩላቸው ÷ በዞኑ 32 ሺህ ሄክታር መሬት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ከፍ ባሉ የቅመማ ቅመም ምርቶች መሸፈኑን አንስተዋል፡፡

በምናለ አየነው