Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ምክር ቤቱ ኢትዮጵያውያን  በጦርነት የተጎዱ  ወገኖችን ለማቋቋም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሳንከፋፈል በጦርነት የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋም እጃችንን ልንዘረጋ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጅ ኢብራሂም ቱፋ ÷ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል በተደረገው ስምምነት የምስጋና እና የደስታ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም  የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ግጭት በሰላም ስምምነት በመጠናቀቁ በመላውኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ስም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

አሁን ከትንሹ ዘመቻ ወደ ትልቁ ዘመቻ ተሸጋግረናል ያሉት ሼህ ሀጅ ኢብራሂም ÷ ትንሹ ዘመቻም ያሳለፍነው ጦርነት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ትልቁ ዘመቻ  እና  ከሁላችን የሚጠበቀው ደግሞ በጦርነቱ  የተፈናቀሉ ወገኖችን ማቋቋም ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ስለሆነም  ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በብሔር ሳይከፋፈል ለተጎዱ  ወገኖች ሊደርስላቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡

 

ለዚህም የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ሁሉም  ዜጋ  እና ባለ ድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ  አቅርበዋል፡፡

 

 

ከአመታት ውጣ ውረድ በኋላ የተገኘው ሰላም ዘላቂነቱ ተጠብቆ ፍሬያፈራ ዘንድ ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለበትም በመግለጫው ተጠቁሟል።

 

 

በሳሙኤል ወርቃየሁ

 

Exit mobile version