Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በቤታቸው ሆነው የሚሰሩና ወደ ቢሮ የሚገቡ ሰራተኞችን ይፋ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በቤታቸው ሆነው የሚሰሩና ወደ ቢሮ የሚገቡ ሰራተኞችን ለይተው ይፋ እያደረጉ ነው።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ ሚኒስቴሩ በቤታቸው ውስጥ በኢሜል እና በስልክ ስራቸውን ማከናወን የሚችሉ እንዲሁም የሚኒስቴሩን የትራንስፖርት የማይጠቀሙ ሰራተኞች ከቤታቸው ሆነው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ወስኗል።

በዚህም መሰረት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ካሉ 377 ሰራተኞች ውስጥ 86 ስራ እንዲገቡ፣ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ካሉት 328 ሰራተኞች መካከል 19 ስራ እንዲገቡ፣ ብሄራዊ ቴአትር ካሉት 307 ሰራተኞች 14 ስራ እንዲገቡ፣ በስፖርት ኮሚሽን ካሉት 218 ሰራተኞች 42 ስራ እንዲገቡ እንዲሁም በሆቴልና ቱሪዝም ድርጅት ካሉት 215 ሰራተኞች 28 ስራ እንዲገቡ የወሰነ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ ከቤት ሆነው ስራ እንዲያከናውኑ ተደርጓል ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአጠቃላይ ካሉት ሰራተኞች ውስጥ 86 በመቶው ከቤታቸው፤ ከቀሪው 14 በመቶ ቢሮ ገብተው እንዲሰሩ መወሰኑን የገለፁት ዶክተር ሂሩት፥ እነዚህ ሰራተኞች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ሰርቪስ የሚጠቀሙ ይሆናል ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በዋናው መስሪያ ቤት ካሉት አጠቃላይ 520 ሰራተኞች 128 ወይም 25 በመቶ ብቻ ቢሮ ገብተው አገልግሎት እንዲሰጡ፤ ቀሪው 75 በመቶ ሰራተኞች ከቤት እንዲሰሩ ውሳኔ አሳልፏል።

አዲስ አበባ ተቀማጭ የሆኑ የዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና ኤምባሲዎች ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት በዲጂታል መልኩ እንዲቀጥል አስፈላጊው መረጃ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

ግብርና ሚኒስቴርም ካሉት ሰራተኞች 80 በመቶ የሚሆኑትን ለ 15 ቀናት በቤታቸው እንዲያርፉ እና እጅግ አስፈላጊ ለሆኑ መንግስታዊ ስራዎች ደግሞ 20 በመቶ የሚሆኑትን ሰራተኞች ለቀጣይ 15 ቀናቶች የሚያሰራ ሲሆን፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከተሉትን ምክረ ሀሳቦች በማኔጅመንት ወስኗል።

በቢሮ እንዲሰሩ የተደረጉ ሰራተኞች 20 በመቶ የሚሆኑት እና ለበርሃ አንበጣ ቁጥጥር መስክ ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች እስፈላጊውን የመከላከል ስራ እና የማህበራዊ ርቀትን ጠብቀው እንዲሰሩ በሽታውን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በቢሮ የተሰራጩ ስለሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስታውቋል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር ከዋናው ግቢ 617 ሰራተኞች ውስጥ 119 በማስቀረት፣ በተጠሪ ተቋማት የሀገር አቀፍ ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ከ215 ሰራተኞች 62 ሰራተኞች በማስቀረት እንዲሁም ከትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ሙሉ በሙሉ የምርት ተግባሩን እንዲቆም በማድረግ ከ712 ሰራተኞች ውስጥ 15ቱን ሰራተኞች ለተለያዩ ስራዎች እንዲቆዩ በማድረግ በአጠቃላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት አሁን ካላቸው 1 ሺህ 544 ሰራተኞች ውስጥ 196 ማለትም 12 ነጥብ 7% በመቶ ብቻ በማስቀረት 1 ሺህ 348 ማለትም 87 ነጥብ 3 በመቶ ሰራተኞች በቤታቸው ሆነው ስራቸውን እንዲሰሩ ውሳኔ አሳልፏል።

የጤና ሚኒስቴርም ነፍሰ ጡር የሆኑ፤ ተላላፊ ያልሆነና የታወቀ በሽታ ህክምና ክትትል እያደረጉ ያሉ ሰራተኞች፣ወደ ጡረታ እድሜ የተጠጉ ሰራተኞችና የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰራተኞች በቤታቸው ሆነው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ውሳኔ አሳልፏል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም በዋናው መስሪያ ቤት ለየዕለት የስራ እንቅስቀሴ እጅግ አስፈላጊ ናቸው ተብለው ከተለዩ 15 ሠራተኞች በስተቀር 90 በመቶ ሠራተኞች ከቤታቸው ሆነው ከቅርብ ኃላፊዎቻቸው ጋር በሚደረጉ የስልክና የኢሜል ልውውጦች የሚሰሩ እንደሚሆን ተገልጿል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰጡት መመሪያ መሠረት፣ አማካሪዎችን ጨምሮ ከ289 የጽህፈት ቤቱ ሠራተኞች መካከል 184 ሠራተኞች ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ከቤታቸው ሆነው ሥራቸውን የሚከውኑ ይሆናል።

ይህም ከቤት ሆኖ የሚሠራውን ሠራተኛ ከአጠቃላዩ 64 በመቶ እንደሚያደርገውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ የፌደራል መንግስት ሠራተኞች በቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ የተላለፈው ውሳኔ ተቋሙን የማይመለከት መሆኑን በማሳወቅ፤ ሁሉም ሰራተኞች በመደበኛ ስራቸው ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የፌደራል መንግስት ሠራተኞች በቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላለፈው ውሳኔ እንደማይመለከተው አስታውቋል።

በመሆኑም ሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች ክፍት መሆናቸውን እና የተለመደውን የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

Exit mobile version