አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት የሐረሪ ክልል የጤናውን ዘርፍ ተደራሽ ለማድረግ የሚያከናውናቸውን ተግባራት እንደሚደግፍ ገለጸ፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ኃላፊ ዶክተር ቡሬማ ሳምቦ የተመራው ልዑክ በሐረሪ ክልል ተገኝቶ በእናቶችና ሕጻናት ጤና፣ እንዲሁም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላይ የተከናወኑ ተግባራትን ጎብኝቷል።
ልዑኩ በጁገል ሆስፒታል ተገኝተው የኩላሊት ማጠቢያ የክፍሉን አገልግሎት አሠጣጥ መመልከታቸውም ተጠቁሟል፡፡
የሸንኮር ወረዳ ጤና ጣቢያ የቀዶ ጥገና ክፍልን መመልከታቸውንም ነው የሐረሪ ጤና ቢሮ መረጃ ያመላከተው፡፡
በጉብኝት መርሐ-ግብሩ የእናቶችና ሕጻናት ጤና ፣ ሥርዓተ ምግብ ፣ የሕጻናት ክትባትና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በክልሉ ጤና ቢሮ የተሰሩ ሥራዎች ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በሐረሪ ክልል የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ የበጀት እና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከድርጅቱ በተገኙ ድጋፎች ለኅብረተሰቡ ጥሩ የሕክምና አገልግሎቶችን መሥጠት እንደተቻለም ነው የገለጹት።
በተለይም በእናትቶችና ሕጻናት ጤና እንዲሁም በኮቪድ-19 ክትባት አሰጣጥ ላይ የተጠናከረ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ኃላፊ ዶክተር ቡሮማ ሳምቦ በበኩላቸው ÷ ላለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ እስከ 30 ሚሊየን ብር በሚደርስ ወጪ የግንባታ ሥራዎችን ማከናወናቸውን ጠቁመዋል።
በቀጠይም የዓለም ጤና ድርጅት ለክልሉ የሚያደርገውን የተለያዩ ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።