አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለጤናዎ ሊያደርጉ ከሚችሉት ነገሮች አንዱና ዋነኛ ነው።
የማያቋርጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በሰው ልጆች ጤና እና የአኗኗር ዘይቤ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ጤናማ የሰውነት ክብደትና ጥንካሬን በማላበስ ለከባድ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድልን እንደሚቀንስም የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የመነቃቃት ስሜትን በመፍጠርና ከፍ ለማድረግ፣ የአዕምሮ ጤናን በመጠበቅ፣ የተስተካከለ እንቅልፍ ለማግኘትና መሰል የጤና በረከቶች እንዳሉት ያነሳሉ።
የተለመዱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ማለትም ኤሮቢክስ፣ ለጥንካሬ የሚሰሩ እንቅስቃሴዎች፣ ካሊስቲኒክስ ወይም የእንቅስቃሴ መሳሪያዎችን የማያስፈልጓቸው መሳሪያዎች (ፑሽ አፕ፣ ሲት አፕ፣ ፑል አፕ)፣ መተጣጠፍና ሌሎችን ያካትታሉ።
እነዚህን የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች እንደየግለሰቡ ፍላጎት ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን ወይንም በግል መስራት ይችላል፡፡
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከመጀመርዎ በፊት እነዚህን ነገሮች ማስተዋል ያስፈልጋል
የጤና ሁኔታን ማረጋገጥ፡- የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከመጀመርዎ በፊት ምን አይነት የጤና ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑ ሊያውቁ ይገባል፡፡
ምክንያቱም እንደየግለሰቡ የጤና ሁኔታ ባለሙያዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች የሚመክሩበት ሁኔታና በጭራሽ እንዳይሰሩ የሚመከሩባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እንቅስቃሴ ከመጀመርዎ በፊት የጤና ሁኔታን ማወቅ የትኛውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባደርግ ለእኔ ይጠቅመኛል ለሚለው ጥያቄዎ መልስ ያገኙበታል፡፡
እቅድና ግብ ማስቀመጥ፦ በመደበኛነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለመጀመር ከወሰኑ በኋላ እቅድና ግብን በማስቀመጥ ጥረትዎን ባሰቡት መልኩ ማሳካት ይችላሉ፡፡
በዚህም ግብዎ 1 ኪሎ ሜትር በመሮጥ መጨረስ ከሆነ በአጭር ርቀት መጀመር ፤ ከዚያም በየጊዜውና በእቅድዎ መሰረት የርቀቱን መጠን በመጨመር ማሻሻል ይቻላል፡፡
ልምምድ ማድረግ፦ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎ ጋር ማጣጣም ለሚደርሱበት ግብ አስፈላጊ ነው።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቀላል ለማድረግ አዘውትሮ መስራትና የህይወትዎ አንድ አካል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የዘርፉ ባለሙያዎች አንድ ግለሰብ ቢያንስ በሣምንት 150 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
ይሁን እንጂ ቀስ ብሎ መጀመርና ሰውነትዎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲላመድ ማድረግ አስፈላጊ ነውም ይላል ኸልዝላይን፡፡