የሀገር ውስጥ ዜና

የትራማዶል መድሀኒት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ ነው

By Amele Demsew

November 01, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራማዶል መድሀኒት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በመድሀኒቱ አጠቃቀም ዙሪያ በሰጠው መግለጫ ከጤና ባለሙያ ትእዛዝ ውጭ በርካታ አፍላ ወጣቶች ለህመም ማስታገሻ በሚል ያለአግባብ እንደሚጠቀሙት መረጃ እንደደረሰው አስታውቋል።

መድሀኒቱ ያለማዘዣ ከሚሰጡ መድሀኒቶች ውስጥ አንዱ እንደነበር የገለፀው ባለስልጣኑ የመድሐኒቱን ሱስ የሚያስይዝ ባህሪ ከግምት ውስጥ በማስገባት ያለማዘዣ ከሚታዘዙ መድሀኒቶች ዝርዝር ውስጥ ለማውጣት የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።

ለዚህም የሁኔታውን አሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባት በመድሀኒቱ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሆነ ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡

መድሃኒቱ ለጤናው ዘርፍ መሰረታዊ መድሀኒት በመሆኑ ከዚህ በኋላ በልዩ ማዘዣ ወረቀት እንደሚታዘዝ እና የመድሃኒቱ ማዘዣም ቁጥጥር እንደሚደረግበት ነው የተገለጸው።

የመድሃኒት ችርቻሮ ድርጅቶችና የጤና ተቋማት በመድሃኒቱ አጠቃቀም ላይ በየጊዜው ሪፖርት እንዲያቀርቡ ይደረጋልም ተብሏል።

ባለሰልጣኑ መድሀኒቱን አለግባብ የሚሸጡ፣ የሚያሰራጩ እና የሚጠቀሙ አካላት ለይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም ነው ያስታወቀው።

በቅድስት አባተ