አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ 3 ነጥብ 7 ሚሊየን አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ማሳ እያለሙ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በመኽር ከለማው 13 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ 46 ከመቶው በኩታ ገጠም የለማ ነው፡፡
አርሶ አደሩ ተቀናጅቶ በኩታ ገጠም ማልማቱ ምርቱን በእጥፍ በመጨመር ከራሱ አልፎ ለገበያ የማቅረብ እድልን እንደፈጠረለት አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ ሰብሎች፣ አትክልት እና ፍራፍሬዎች በኩታ ገጠም እየለሙ መሆኑን ገልጸው÷ በቀጣይ ለአኩሪ አተር እና ሩዝ ሰብሎች ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
በኩታ ገጠም ለሚያለሙ አርሶ አደሮች ኢንስቲትዩቱ የግብዓት፣ የቴክኒክ እና የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮች በበኩላቸው÷ ለየአከባቢያቸው ስነ-ምህዳር ተስማሚ እና ምርታማ የሚያደርጉ የሰብል ዝርያዎችን በመጠቀም ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በአልማዝ መኮንን