አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ህወሓት ምክንያት ጉዳት ደርሶበት በጥገና ላይ የነበረው የወልዲያ -አላማጣ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮች የቴክኒክ ድጋፍ ሥራ አስኪያጅ ተስፋዬ መንግስቴ እንደገለጹት÷ ዛሬ ያለዕረፍት በተሠራው የጥገና ሥራ የማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና እና የተሰበሩ ኢንሱሌተሮች ቅየራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ መስመሩን መፈተሽ ተጀምሯል፡፡
በተቋሙ የማስተላለፊያ መስመሮችና የማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ሀብታሙ ውቤ በበኩላቸው÷ በጥገና ሥራው ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ከሦስት ሣምንት ያላነሰ ጊዜ የሚፈልገውን ሥራ በአንድ ሣምንት ማጠናቀቅ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ከወልዲያ እስከ አላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ ድረስ ያለው መስመር ጥገና መጠናቀቅ÷ ከአላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ በ66 ኪሎ ቮልት ኃይል ሲያገኙ የነበሩት ላሊበላ፣ ሰቆጣና ቆቦ እንዲሁም ማይጨው እና አካባቢያቸው ኃይል እንዲያገኙ ያስችላል መባሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ አመላክቷል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!