Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ በጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ የጋራ በሆኑ የሁለትዮሽ ጉዳዮቻቸው ላይ በትብብር ለመስራት ተስማሙ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ  ታገሰ ጫፎ ከሞዛምቢክ ሪፐብሊክ ምክር ቤት አቻቸው ላውሪን ፍራንሲስኮ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይታቸው በዋናነት የሰላምና ደህንነት ፈተናዎች በሆኑት በተለይም ሽብርተኝነትና የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በትብብር መስራት አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህ ወቅት አፈ ጉባኤዎቹ በየሀገራቱ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፥ በሁለቱ ምክር ቤቶች መካከል ያለውንብ ትብብር ለማጠናከርም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በዋናነትም እንደ የአፍሪካ፣ የካሪቢያን እና የፓሲፊክ  ሀገራት መንግስታት ፓርላማ ባሉ የባለብዙ ወገን መድረኮች በትብብር መስራት በሚቻልበት አግባብ ላይ መምከራቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ከሞዛምቢክ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ናት ያሉት አፈ ጉባኤው÷ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን ማፈላለግ አስፈላጊ መሆኑን  አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራ ልዑክ በ61ኛው የአፍሪካ፣ የካሪቢያን እና የፓሲፊክ ግዛቶች የፓርላማ ጉባኤ ለመሳተፍ በሞዛምቢክ ማፑቶ ይገኛል።

Exit mobile version