ጤና

የጡት ካንሰር መንስዔው እና ምልክቶቹ

By Meseret Awoke

October 27, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ካንሰር ከሰውነታችን ቁጥጥር ውጪ የሆነ የህዋሳት መብዛት ሲኖር የሚከሰት በሽታ መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ለአብነት የጡት ካንሰር በሽታ በጡት ውስጥ ያሉ ሴሎች ከቁጥጥር ውጪ መራባት እንዲሁም አይነታቸውን ቀይረው ሲራቡ ይከሰታል፡፡

የጡት ካንሰር መንስዔው በርካታ እንደሆነ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የጠቅላላ ቀዶ ህክምና ሃኪም ዶክተር ህይወት የሺጥላ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ሴት መሆን በራሱ፣ በቤተሰብ ውስጥ የጡት ካንሰር ታማሚ ካለ ወይም በዘረመል ፣ የኑሮ ዘይቤ፣ ከመጠን በላይ ውፍረት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የጡት ካንሰር በሽታ ምልክቶቹ ደግሞ የጡት መጠን መለያየት፣የጡት እብጠት(ሁሉም እብጠት ግን ካንሰር አይደለም)፣ ከጡት ጫፍ የሚወጣ ፈሳሽ (በተለይ ደም የቀላቀለ)፣የብብት ውስት እብጠት፣ የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መሰርጎድ ፣ የጡት መሰርጎድ እና የጡት ቆዳ ቀለም መቀየር መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ሴት ልጅ እራሷን በየጊዜው መፈተሸ አለባት ያሉት ዶክተር ህይወት፥ ይህም ማለት መስታወት ፊት በመቆም የጡቶቿን መጠን ማየት፣ ብብት አካባቢዋን በየጊዜው ማየት፣ ያበጡ ነገሮች ካሉ ማየት እና በአጠቃላይም የጡት ሁኔታን መከታተል ያስፈልጋል ሲሉ ይመክራሉ፡፡

የምታጠባ እናት ከሆነች ደግሞ ካጠባች በኋላ ወይም ወተቱን አልባ ጡት ባዶ ከሆነ በኋላ ብትፈትሽ ይመረጣል፤ እንዲሁም የማታጠባ ሴት ከሆነች የወር አበባዋ ከመጣ ከአምስት እስከ ሰባት ባሉ ቀናት ውስጥ ብትፈትሽ ይመከራል ነው ያሉት፡፡

በዚህም የተለየ ነገር ካዩ ወይም ጥርጣሬ ካደረባቸው ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

እድሜያቸው ከ40 በላይ የሆኑ ሴቶች ፣ በቤተሰባቸው የጡት ካንሰር ታማሚ ያለ ሴቶች ደግሞ በየጊዜው የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባቸው መክረዋል፡፡

ጡት ካንሰር ሴት ላይ ብቻ የሚከሰት ብቻ ሳይሆን ወንድም ላይ የመከሰት ዕድል ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ ብሎም በዓለም አሳሳቢ የሆነ እና በአጠቃላይ ከካንሰር በሽታዎች ወስጥ በሞት ምጣኔ አምስተኛ ደረጃ ላይ ያለ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በፌቨን ቢሻው