አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአላማጣ እስከ ቆቦ እየተከናወነ ያለው የኤሌክትሪክ መስመር ጥገና 50 በመቶ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት የተጎዱ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን የመጠገን ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የወልዲያ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ወልደሰማያት ገልፀዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት የጥገና ስራው እየተከናወነ የሚገኘው ከአላማጣ እስከ ቆቦ እና ከአላማጣ እስከ ላሊበላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከአላማጣ እስከ ቆቦ እየተከናወነ የሚገኘው የመካከለኛ መስመር የጥገና ስራ 50 በመቶ መጠናቀቁንና የ66 ኪሎ ቮልት የትራንስሚሽን መስመር ጥገና ስራም መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
የጥገና ሥራው በሁለት ምድብ ተከፍሎ እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት አቶ ሽመልስ ፥ ከ40 እስከ 50 የሚደርሱ የዲስትሪክቱ ሠራተኞች እየተሳተፉበት እንደሚገኝና በአንድ ሣምንት ጊዜ ውስጥ ጥገናውን ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአካባቢው በሚገኙ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እንደደረሰባቸው መግለጻቸውን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በዚህም በሰሜን ወሎ አካባቢ አስር የኤሌክትሪክ ኮንክሪት ምሰሶዎችና ከ46 ትራንስፎርመሮች በላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ነው የተናገሩት።
ከዚህ ባለፈም በአካባቢው ለመስኖ ፕሮጀክት የተተከሉ የእንጨት ምሰሶዎች ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም ፥ በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች የገቡ የዛፍ ቅርንጫፎችን የሚመለከታቸው የአስተዳድር አካላት ህብረተሰቡን በማስተባበር የምንጣሮ ስራ እንዲያከናውኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!