Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የብሔራዊ ስታዲየም ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ማስጀመር የሚያስችል የፊርማ ስነ ስርዓት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ ስታዲየም ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታን ለማስጀመር የሚያስችል የፊርማ ስነ ስርዓት ተካሄደ።

በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ በቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ስራ ተቋራጭነት በኤም ኤች ኢንጅነሪንግ አማካሪነት እየተገነባ የሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተገነባ ይገኛል።

ሁለተኛውን ምዕራፍ ግንባታ ማስጀመር የሚያስችለውን የፊርማ ስነ ስርዓትም በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን ከተቋራጭ ድርጅቱ ጋር ተፈራርሟል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ከስታዲየሙ ሜዳ ሳር የማልበስና የመሮጫ ትራክ በስተቀር በውሉ መሠረት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቋል።

የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ደግሞ የመጫወቻ ሜዳውን ሳር ማልበስ፣ የመሮጫ ትራክ ማንጠፍ፣ የስታዲየሙን ጣሪያ ማልበስና ወንበር መግጠም፣ ሰው ሰራሽ ሀይቅ፣ የሄሊኮፕተር ማረፊያ፣ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራ፣ ሳውንድ ሲስተም፣ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች፣ የመለማመጃ ሜዳዎች እና ሌሎች ስራዎችን የሚያጠቃልል ይሆናል ተብሏል።

ለግንባታው 5 ነጥብ 57 ቢሊየን ብር የተመደበ ሲሆን ስታዲየሙን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግ ከስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

 

 

 

Exit mobile version