አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፍራፍሬና አትክልት የሚገኘው ቫይታሚን ሲ የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም ለማሳደግ ይረዳል።
ቫይታሚን ሲ የደም ግፊት መቀነስን ጨምሮ ብዙ የጤና ጠቀሜታዎች አሉት።
ቫይታሚን ሲ ሰውነት ማምረት የማይችለው አስፈላጊ ቫይታሚን ሲሆን፥ በርካታ የጤና ጥቅሞች አሉት።
እንደ ብርቱካን፣ እንጆሪ፣ ኪዊ ፍሬ፣ ቃሪያ፣ ብሮኮሊ፣ ጎመን እና ሰላጣን ጨምሮ በብዙ ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች ውስጥ የሚገኘው ቫይታሚን ሲ በውሃ ውስጥ በሚሟሟ ንጥረ ነገር መልክም ይዘጋጃል።
የጤና ባለሙያዎች ግን በውሃ ውስጥ ከሚሟሟው ንጥረ ነገር ይልቅ ቫይታሚን ሲን ከምግብ ማግኘቱ የተሻለ መሆኑን ይመክራሉ።
በቀን ውስጥም ለሴቶች 75 ሚሊ ግራም ለወንዶች ደግሞ 90 ሚሊ ግራም ቪታሚን ሲ መውሰድ እንደሚገባም ነው የሚገልጹት።
የቫይታሚን ሲ ጥቅሞች
ሥር የሰደደ በሽታ የመያዝ እድልን ለመቀነስ
ቫይታሚን ሲ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚጨምሩ ሞለኪውሎች የያዘ በመሆኑ እንደ የልብ ሕመም ያሉ ሥር ለሰደዱ በሽታዎች የመጠቃት እድልን ይቀንሳል።
የደም ግፊትን ለመቆጣጠር
ከፍተኛ የደም ግፊት ላለባቸው ሰዎች የደም ፊትን ለመቀነስ ይረዳል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተደረገ ጥናትም ቫይታሚን ሲ የደም ቧንባዎች ስራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ በማድረግ የደም ግፊትን ለመቀነስ እንደሚረዳ አመላክቷል።
የልብ በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ፦ በተደረገ ጥናት ቪታሚን ሲ በተለይ ከ500 እስከ 700 ሚሊ ግራም በቀን የሚወስዱ ሰዎች የልብ በሽታ ተጋላጭነታቸው በ25 በመቶ ቀንሷል ነው የተባለው።
ይህም አላስፈላጊና ለጤና ጎጂ የሆነውን የኮሌስትሮል ክምችትን ለማስወገድ እንደሚረዳም ነው ባለሙያዎቹ የሚገልጹት።
በደም ውስጥ ያለው የዩሪክ አሲድ መጠን ለመቀነስ እና በሪህ መጠቃትን ለመከላከል
በቫይታሚን ሲ የበለፀጉ ምግቦች በደም ውስጥ ያለው የዩሪክ አሲድ መጠን እንዲቀንስ እና የሪህ በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ይረዳሉ።
ሰውነት የብረት እጥረት እንዳያጋጥመውነ የደም ማነስን ለመከላከል
ቫይታሚን ሲ ስጋ-ነክ ካልሆኑ ምግቦች የሚገኘውን በደንብ ያልተዋሃደ ብረት ሰውነት እንዲያገኝ ይረዳል።
ይህን ያልተዋሃደ ብረትም ለሰውነት ጠቃሚ ወደሆነ ውህድ መቀይርም የቫይታሚን ሲ ሌላኛው ጥቅም ነው።
ከዚህ ባለፈም በብረት እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን ደም ማነስ ለመከላከል ይረዳል።
በሽታ የመከላከል አቅምን ለማሳደግ
ቫይታሚን ሲ ነጭ የደም ሴሎችን ቁጥር በማብዛት የሰውነትን የበሽታና የኢንፌክሽን መጠቃት እድልን ይቀንሳል።
ከዚህ ባለፈም የነጭ የደም ሴሎችን ውጤታማነት በማሳደግ፣ የቆዳን ተጋላጭነት በመቀነስ እና ቁስል በፍጥነት እንዲድን በመርዳት በሽታ የመከላከል አቅምን ይጨምራል።
የማስታወስ ችሎታ እንዳናጣ
ቫይታሚን ሲ ከእድሜ መጨመር ጋር ተያይዞ የሚከሰትን የማስታወስና የማገናዘብ ችሎታ ማጣትን ለመከላከል ይረዳል።
ቪታሚን ሲ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ብሎም የማስታወስና የማገናዘብ አቅምን የሚጎዱ ሁኔታዎችን ለማስወገድና ለመከላከል እንደሚረዳ ጥናቶችን ዋቢ ያደረገው የኸልዝ ላይን መረጃ ያመላክታል።
በተጨማሪም እንደ ጉንፋን፣ አላስፈላጊ የኮሌስትሮል መጠንን ለማስወገድ፣ መርዛማ ነገሮችን ከሰውነት ለማጥፋት እና የካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስ እንደሚረዳ የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።