Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

መንግስት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር ድምጻቸውን ላሰሙ ለመላው ኢትዮጵያውያን ምስጋና አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር ድምጻቸውን ላሰሙ ለመላው ኢትዮጵያውያን ምስጋና አቅርቧል፡፡

አገልግሎቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ÷ትናንት እና ዛሬ “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምፄንም አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል በመላው ኢትዮጵያ ባሉ ከተሞች በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ህዝባችን በሀገሩ ሉዓላዊነት እና ክብር እንደማይደራደር ድምፁን ከፍ አድርጎ አሰምቷል ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በህዝብ የተመረጠ በመሆኑ ለሚንፀባረቁ የህዝብ ፍላጎቶች እውቅና እንደሚሰጥ የጠቆመው መግለጫው÷ የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገር ሉዓላዊነት እንደማይደራደር ሲገልፅ የቆየው ከዚሁ ህዝባዊ ፍላጎት በመነጨ እሳቤ እንደሆነ ወዳጅም ጠላትም ሊገነዘበው ይገባል ነው ያለው።

መንግስት ÷ የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገሩ ሉዓላዊነት እና ክብር ያለውን ቀናዒነት በትልልቅ ህዝባዊ ሰልፎችና ትዕይንቶች በመግለፁ አድናቆት እና ክብር እንዳለውም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በቀጣይም የኢትዮጵያ ሕዝብ በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያንን በጋራ በሚያስተሳስሩ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ አንድነቱን እንዲያሳይ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል ፡-

ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር ድምፃችሁን ላሰማችሁ ለመላው ኢትዮጵያዊያን መንግስት ምስጋናውን ያቀርባል!!

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ ጉዳይ እንደማይደራደር ዛሬም በይፋ አስታውቋል። ትናንት እና ዛሬ “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምፄንም አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል በመላው ኢትዮጵያ ባሉ ከተሞች በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ህዝባችን በሀገሩ ሉዓላዊነት እና ክብር እንደማይደራደር ድምፁን ከፍ አድርጎ አሰምቷል።በመላው የአገራችን ትልልቅ ከተሞች የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ሀገሩን ለማንም አሳልፎ እንደማይሰጥና ማንኛውንም የዉጭጣልቃ ገብነት እንደማይቀበል ገልጿል።
ይህ የህዝብ ድምፅ በሚገባ ሊሰማ ይገባል። ህዝባችን ያሰማው ድምፅ የኢትዮጵያ ድምፅ ነው። ኢትዮጵያ በምንም መልኩ በውስጣዊ ጉዳይዋ ላይ ማንም ጣልቃ እንዲገባባት የማትፈልግ ሉዓላዊ ሀገር ናት። ኢትዮጵያዊያን ዛሬም እንደ ትላንቱ በማንኛውም ሁኔታ በየትኛውም የውጭ ኃይል የሀገራቸው ሉዓላዊነት እንዳይደፈር ዘብ እንደሚቆሙ ዳግም አረጋግጠዋል፡፡
ሉዓላዊነታችን ይከበር፣ በሰብዓዊ መብት ስም ጣልቃ ገብነት ይቁም፣ የተልዕኮ ጦርነት ይብቃ፣ ወዘተ የሚሉ መልእክቶችንም አሰምተዋል፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ለኢትዮጵያ እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ሀገራችን ላይ የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ አንዳንድ ምዕራባውያን ተቋማት፣ ግለሰቦች እና ሚዲያዎች የሚያራምዱትን የተሳሳተ አቋም ህዝባችን በመላው ሀገሪቱ ተቃውሟል። የትግራይ ህዝብ ጥቅም እና ፍላጎት ከወገኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ውጪ በህወሓት ሊከበር እንደማይችልም ህዝባችን በይፋ ተናግሯል። መከላከያ ሠራዊታችን ለግዛት አንድነት እና ለሉዓላዊነታችን የሚያደርገውን ተጋድሎም ደግፏል፡፡
አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ተቋማት እና አመራሮች ሀገራችን ላይ የከፈቱት የሀሰት ዘመቻ በሀገራችን ሰላምን እንደማያመጣም የኢትዮጵያ ህዝብ በሰልፎቹ ተናግሯል። በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ያለውን መንግስት መደገፍ እና አሸባሪውን ህወሓትን ማውገዝ እንደሚገባም ህዝቡ በድምፁ አስተጋብቷል።
ይህም መደመጥ ያለበት የህዝብ ፍላጎት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎቱን የገለፀውና ለመግለፅ እየተዘጋጀ የሚገኘው በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሃገራትም ጭምር ነው። በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና በአውስትራሊያ ከተሞች የሚገኙ የኢትዮጵያ ልጆችም የሀገራቸውን ድምፅ በከፍተኛ ደረጃ እያሰሙ ነው።
ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የተናገሩት የሀገራቸውን ፍላጎት በመሆኑ ምዕራባዊያን መንግሥታት ይህንን ድምፅ በሙሉ ልባቸው ሊያዳምጡት ይገባል። እነዚህ ሰልፎች የኢትዮጵያ ህዝብ በፖለቲካ አመለካከት፣ በኢኮኖሚ ደረጃ፣ በሀይማኖት እና በብሔር ሳይለያይ በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ መቆሙን የሚያመለክቱ ናቸው። በኢትዮጵያ ምድር በሀገሩ ሉዓላዊነት ከህፃን እስከ አዋቂ የሚደራደር አለመኖሩንም በተጨባጭ የሚያሳዩ ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በህዝብ የተመረጠ በመሆኑ ለሚንፀባረቁ የህዝብ ፍላጎቶች እውቅና እንደሚሰጥ ለመግለፅ ይወዳል። የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገር ሉዓላዊነት እንደማይደራደር ሲገልፅ የቆየው ከዚሁ ህዝባዊ ፍላጎት በመነጨ እሳቤ እንደሆነ ወዳጅም ጠላትም ሊገነዘበው ይገባል።መንግሥት በምንም መልኩ በህዝብ ፍላጎት እና በሀገር ሉዓላዊነት ላይ እንደማያቅማማ ከዚህ ቀደም እንዳስታወቀው ሁሉ አሁንም ዳግም ያረጋግጣል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገሩ ሉዓላዊነት እና ክብር ያለውን ቀናዒነት በትልልቅ ህዝባዊ ሰልፎችና ትዕይንቶች በመግለፁ መንግሥት ያለውን አድናቆት እና ክብር እየገለፀ፤ ወደፊትም በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያንን በጋራ በሚያስተሳስሩ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ አንድነቱን እንዲያሳይ ጥሪውን ያቀርባል።
ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Exit mobile version