አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ይረዳሉ በተባሉ ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ እና ጥራቱና ምንጩ ያልተረጋገጠ ምርት ሲሸጡ በነበሩ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን በዚህ ተግባር በተሰማሩ 37 መድሀኒት መደብሮች ላይ የማሸግ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
ከዚህ ባለፈም 24 ለሚሆኑት ደግሞ ማስጠንቀቂያ መስጠቱንም ነው ያስታወቀው።
የመድሃኒት መደብሮቹ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዱ ቁሳቁሶችን በተጋነነ ዋጋ በማቅረብ፣ ምንጩ ያልታወቀ ምርት በመሸጥና ምርቱ እያለ የለም ሲሉ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ 940 የመድሃኒት መደብሮች መካከል በ725ቱ ላይ ቁጥጥር መደረጉን፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደብረወርቅ ጌታቸው ተናግረዋል።
በተደረገው ቁጥጥር የተጋነነ ዋጋ ያቀረቡ፣ ምንጩ ያልታወቀ ምርት የሸጡና ምርቱ እያለ የለም ሲሉ በነበሩ 37 የመድሃኒት መደብሮች ላይ የማሸግ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት።
ሁለት የሳሙናና የዲተርጀንት አቅራቢነት ፈቃድ ያላቸው ግለሰቦች የእጅ ማጽጃ ኬሚካል (ሳኒታይዘር) እና የእጅ ሳሙና እናመርታለን በሚል ሲያታልሉ በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር ውለዋልም ነው የተባለው።
በትእግስት አብርሃም
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision