አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕዳር ከተማ ነዋሪዎች በሰብዓዊ እርዳታ ስም የሚደረግ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም እና በውክልና ጦርነት መጠቃት እንዲያበቃ ጠየቁ፡፡
ባሕርዳር ከተማ የምዕራባውያንን ያልተገባ ጣልቃገብነት እና አሸባሪው ህወሓትን የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡
በሕዝባዊ ሰልፉ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ግርማ የሺጥላን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የሰልፉ ተሳታፊዎች አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ ሉዓላዊነታችንን አክብሩ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
“ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምፄን አሰማለሁ” በሚል መሪ ሐሳብ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ ሰልፍ የውክልና ጦርነት ሊያበቃለት እንደሚባ ተግጿል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰመስተዳደር ይልቃል ከፋለ በሰልፉ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያ ህልውናዋን የምታስከብረው በደም በተከፈለ መስዋዕትነት ነው ብለዋል፡፡
የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን አልደፈርም ባይነት በተግባር እየደገመ ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል÷ የሉዓላዊነታችን መገለጫ የሆነውና የአርበኝነት ስሜት እየጎመራ እንዲሄድ ደሙን እያፈሰሰና አጥንቱን እየከሰከሰ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ እንድታደርጉ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት እያደረገ ያለው ጦርነት የውክልና ጦርነት ለመሆኑ÷ አማራና አፋርን ሲወር ምንም ያላሉ ምዕራባውያን አሁን በመከላከያ ሠራዊት ሲመታ ለምን ብለው በሀገራችን ላይ የሚዲያና የዲፕሎማሲ ጫና እያደረጉ መሆኑ መሳያ ነው ብለዋል፡፡
በአለምሰገድ አሳዬ