አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮምቦልቻ ከተማ አሸባሪው ህወሓትን እና የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡
ሕዝባዊ ሰልፉ የተካሄደው÷ “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መሪ ሐሳብ ነው፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች “በውክልና ጦርነት መጠቃት ይብቃ”፣ “ለዘላቂ ሰላም አሸባሪው ህወሓት ትጥቅ ይፍታ”፣ “የሽብር ቡድኑ ህወሓት ቅጥረኛ ነው” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል፡፡
የትግራዋይ ልማትና ብልፅግና የሚረጋገጠው ከኛ ከወገኖቻቸው ጋር ነው ያሉት የከተማዋ ነዋሪዎች÷ የምዕራባውያን እጅ የረዘመበት የውክልና ጦርነት እንዲበቃ እየጠየቁ ነው፡፡
ለዘላቂ ሰላም አሸባሪው ህወሓት ትጥቅ መፍታት አለበት፣ በዕርዳታ ስም በሉዓላዊነታችን ጣልቃ መግባት ይቁም በማለት ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ሰልፈኞች በኮምቦልቻ ዋናው አደባባይ ተገኝተው ለምዕራባውያንና አሸባሪው ህወሓት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መሀመድ አሚን የሱፍ ባደረጉት ንግግር÷ የወዳጆቻችንን ድጋፍ በቅንነት የምንቀበል የመሆናችንን ያህል በሉዓላዊነታችን የሚመጣ ገደብ አልባ ጣልቃ ገብነትን ደግሞ የማንታገስ ኩሩ ሕዝብ ነን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሰላም ማረጋገጥ የቀጣናውን ሰላም ማረጋገጥ መሆኑን ባላገናዘበ ሁኔታ ጫና ለማሳደር እየሞከሩ ያሉ ምዕራባውያንን እንቃወማለን ነው ያሉት፡፡
በኢሌኒ ተሰማ