የሀገር ውስጥ ዜና

የቦንጋ ዩኒቨርስቲ የሚያከውናቸው የግብርና ሥራዎች ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

By Meseret Awoke

October 22, 2022

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቦንጋ ዩኒቨርስቲ ከመማር ማስተማሩ ሂደት ጋር አያይዞ የሚያከውናቸው የግብርና ሥራዎች ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ ምዕራብ ክልል ቆይታቸው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲን የግብርና ስራዎች ጎብኝተዋል፡፡

ጉብኝታቸውን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዩኒቨርሲቲው በምርምር የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀም ጤፍ፣ ቡና፣ ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎች እና የወተት ተዋጽዖዎችን እያመረተ መሆኑን ገልፀዋል።

የእንስሳት እና የአሣ እርባታም እያካሄደ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም ለህክምና የሚውሉ ዕጽዋት ላይ ምርምር እያደረገ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ይህም የዩኒቨርስቲው እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አብራርተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ያከናወናቸው የግብርና ስራዎች ተግባራት በእጅ ያሉ አቅርቦቶችና ግብአቶችን በውጤታማነት መጠቀምን በተግባር የሚያሳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡