ቢዝነስ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአብራሪነት ያሰለጠናቸውን 236 ሰልጣኞች አስመረቀ

By Alemayehu Geremew

October 22, 2022

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፕላን አብራሪነት ያሰለጠናቸውን 236 ሰልጣኞች አስመረቀ፡፡

አየር መንገዱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአቪየሽን አካዳሚው በክፍል ውስጥና በተግባር ያሰለጠናቸውን አብራሪዎች ነው ዛሬ ያስመረቀው፡፡

በምረቃ ሥነ- ሥርአቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፥ ከባዱን የሥልጠና ጊዜ አጠናቀው ለዚህ ቀን ለደረሱ ተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለውም በአየር በረራ ዘርፍ የደኅነት ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አስምረውበታል፡፡

በመሆኑም ተመራቂዎቹ የተሳፋሪዎችን ደኅንነት ጠብቀው በኃላፊነት የሙያው ሥነ-ምግባር ጠብቀው ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

አየር መንገዱ እስካሁን ከ1 ሺህ 500 በላይ አውሮፕላን አብራሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን፥ በ66 ዓመት የአገልግሎት ጊዜው በአጠቃላይ ከ180 ሺህ በላይ ወጣት የበረራ ባለሙያዎችን አስመርቋል።

በትዕግስት ብርሃኔ