ቴክ

የሳይንስ ሙዚየም ለታዳጊዎች ያለው አበርክቶ

By Feven Bishaw

October 20, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳይንስ ሙዚየም በታዳጊዎች አዕምሮ ውስጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂን ፅንሰሃሳብ ከማስረፁም በላይ ነገ መሆን የሚፈልጉትን ትክክለኛ መሰረት ይዘው እንዲያድጉ መንገድ እንደሚከፍት ይነገራል፡፡

የሳይንስ ሙዚየም መስከረም ወር ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመዲናዋ በይፋ መከፈቱ የሚታወስ ሲሆን÷ሙዚየሙ ኢትዮጵያ በአስገራሚ ፍጥነት በማደግ ላይ ካለው ቴክኖሎጂ ጋር ለመጣመር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይም ነው ተብሎለታል ።

የሙዚየሙን በይፋ መከፈት ተከትሎም ለተከታታይ ሳምንታት ለእይታና ለህዝብ ክፍት ሲሆን÷ በዚኅም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሙዚየሙን በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ፡፡

ሙዚየሙን ሲጎበኙ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ታዳጊዎች ሙዚየሙን በመጎብኘታቸው መደሰታቸውን እና እኔም ሀገርን የሚያስጠራ ስራ በሳይንሱ እና በቴክኖሎጂው ዘርፍ አበረክታለሁ የሚል መነቃቃትን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ከዚህ በላይ እንድንሰራ ያደርገናል፤ መሆን ለምንፈልገው ነገር እገዛ ያደርግልናል፤ ለነገ እራሳችንን ለማዘጋጀት ይጠቅመናል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሙዚየሙን ያልጎበኙ ታዳጊዎችም መጥተው እንዲጎበኙና በርካታ ነገሮችን እንዲመለከቱ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሳይንስ ሙዚየሙ ሀገር በውጣ ውረድ ውስጥ ብትሆንም ካሰበችበት ለመድረስ የዜጎቿን እና የመሪዎቿን ብርታት ብቻ እንደምትሻ ማሳያ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ከጥገኝነት የመላቀቅ ጉዞ ጅማሬ ማጠንጠኛ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላልም ነው የተባለው፡፡

የሳይንስ ሙዚየሙ በመዲናዋ በሰባት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን÷ በኪነ-ህንጻ ንድፍ ውስጥ ያካተተው ክብ ቅርጽም በማያቋርጥ እድገት ውስጥ ያለን እድገትና የሰው ልጆችን ጥበብ የሚያመለክት ነው።