ቴክ

ናይሮቢ በኤሌክትሪክ የሚሰራ የመጀመሪያውን አውቶብስ አስተዋወቀች

By Meseret Awoke

October 20, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኬኒያ መዲና – ናይሮቢ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውንና በኤሌክትሪክ የሚሰራውን አውቶብስ ይፋ አድርጋለች።

‘ፀሃያማዋ አረንጓዴ ከተማ’ በመባል የምትታወቀው ናይሮቢ በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰራ አውቶብስ መጠቀም መጀመሯ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከሉ ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ታምኖበታል፡፡

መቀመጫውን ናይሮቢ ያደረገው ሮም የተባለው ኩባንያ እስከ 77 መንገደኞችን የሚይዝ አውቶብስ ይፋ አድርጓል።

አውቶብሱ 2 ሰአት በኤሌክትሪክ ሃይል ከተሞላ በኋላ ያለ ማቋረጥ 360 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላል ነው የተባለው።

በተጨማሪም በሰዓት 70 ኪሎ ሜትር ፍጥነት እንደሚጓዝም የአፍሪካ ኒውስ መረጃ ያመላክታል።

ኩባንያውም ይህ የኤሌክትሪክ ትራንስፖርት አገልግሎት በኬኒያ ብቻ እንደማይገታ ገልጾ ፥ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ተጠቃሚ ለማድረግ እሰራለሁ ብሏል፡፡

የድርጅቶች የፕሮጀክት አስተባባሪ ዴኒስ ዋካባ እንዳሉትም ፥ የኤሌክትሪክ አውቶብሱ ዜጎችን በአስተማማኝ፣ በምቾት እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገለገሉ ያስችላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በዋናነት የአየር ንብረት ለውጥ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቀነስ እንደሚረዳ ገልጸዋል።