አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2015፣ (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ እና ለስሟ የሚመጥን ገጽታ እንዲኖራት ታልሞ ሲሠራ የቆየው የሸገር ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት በስኬት መጠናቀቁን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ይህ ሥፍራ ለሀገር ኩራት፣ ለጎብኚዎች መዳረሻ፣ ለመዲናችን ነዋሪዎች የዘወትር መገልገያ እንዲሆን መዘጋጀቱንም ነው ያመለከተው።
የሸገር ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት መጠናቀቁን በማስመልከትም፥ ለምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ልዩ ስጦታ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ጽህፈት ቤቱ ጋብቻቸውን ለመፈጸም የተዘጋጁ ወይም አቅደው ሳይሳካላቸው የቆዩ 50 ጥንዶችን በመሥፈርት መርጦ የጋብቻ ሥርዓታቸውን በጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. የወዳጅነት የሠርግ ዐጸድ እንዲፈጽሙ ማቀዱን አመልክቷል።
በመሆኑም መሞሸር ያሰቡ ወይም ሊሞሸሩ አቅደው በልዩ ልዩ ምክንያት ሳይከውኑት የቀሩ በዚህ ዘመናዊ እና ያማረ ስፍራ ሠርጋቸውን ከሚፈጽሙ 50 ጥንዶች መካከል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።
በፕሮጀክቱ ምረቃ ዕለት ሠርጋቸው ከሚፈጸም 50 ጥንዶች አንዱ ለመሆን በshegerprize@pmo.gov.et
ድረገፅ ላይ ለዚሁ የተቀመጠ ቅጽን ሞልተው እስከ ጥቅምት 14፣ 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ድረስ ኢሜይል በመላክ እንዲሳተፉ አሳስቧል።
ቅጹን በሚከተለው ማስፈንጠሪያ ያገኙ፦ https://bit.ly/3SiaUiN