Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ በሕንድ – አፍሪካ የመከላከያ ሃይል ውይይት ላይ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ የተመራው ልዑክ በሕንድ – አፍሪካ የመከላከያ ሃይል ውይይት ላይ በጉጅራት እየተሳተፈ ነው፡፡

ዶክተር አብርሃም በላይ በአፍሪካ-ሕንድ እንዲሁም በኢትዮ-ሕንድ የመከላከያ ጦር ትብብር ላይ ምልከታቸውን ማጋራታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዶክተር አብርሃም ÷ ውይይቱ ኢትዮጵያና ሕንድ በቀጣይ በመከላከያው ዘርፍ አጋርነታቸውን እና ትብብራቸውን ለማጠናከር መደላደል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሕንድ የቀረበላት የተሳትፎ ግብዣ ÷ ሀገራቱ በቀጣይ በመከላከያው ኢንዱስትሪ፣ ቴክኖሎጂ እና ልማት በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን መንገድ የከፈተ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ሀገራቱ የመከላከያ ጦር አቅማቸውን ለማጎልበት በጥምረት ለመስራት እና አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለማማተር ያስችላል የሚል ዕምነት እንዳላቸውም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሳይበር መከላከያ ፣ በባሕር ኃይል እና ደኅንነት እንዲሁም ሽብርተኝነትን መከላከል ላይ ከሕንድ ጋር በጥምረት መስራት እንደምትፈልግም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ የሕንድ መንግስት ለእርሳቸውና ልዑካቸው ላቀረበላቸው ግብዣ እንዲሁም ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።

የሕንድ መከላከያ ሚኒስትር ራጃናት ሲንግ ÷ በውይይቱ ላይ የተገኙትን ተሳታፊዎች አመስግነዋል፡፡

ሕንድ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗንም የሕንድ መከላከያ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል ነው የተባለው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version