አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አየርላንድ የፀጥታው ምክር ቤትና የአውሮፓ ህብረትን በመጠቀም እየፈፀመች ከሚገኘው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከሚነካ ድርጊቷ እንድትታቀብ ኢትዮጵያ ጠየቀች።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለዓየርላንድ የውጭ ጉዳይ እና መከላከያ ሚኒስትር ሳይመን ኮቨኒ ደብዳቤ ፅፈዋል።
አቶ ደመቀ በደብዳቤያቸው ሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ወዳጅነት መስርተው የኖሩ እንደመሆናቸው መጠን አሁን ላይ አየርላንድ እየፈጸመች ያለችው ደባን ኢትዮጵያ ያልጠበቀችው መሆኑን ጠቅስዋል።
በፈረንጆቹ 2018 ላይ በኢትዮጵያ የተገኘውን ለውጥ ተከትሎ በሀገሪቱ እያበበ የመጣው ዴሞክራሲ ያስደነገጠው አሸባሪው ህወሓት፥ ሀይል ሲያሰለጥን ቆይቶ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈፀሙን በደብዳቤያቸው አስታውሰዋል።
ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ግጭት መቀስቀሱን፤ ግጭቱን ለማስቆምም የፌደራል መንግስት ጥረትን ውድቅ እያደረገ ጥቃት እየፈፀመ መኖሩንም ነው ያመለከቱት።
የኢትዮጵያ መንግስት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ደመቀ፥ የአፍሪካ ህብረት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ሁሉ መቀበሉን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በግጭቱ ወቅት ለተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ የሆኑ ወገኖችን በመጠየቁ እና የሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ እንዲደርስ እያደረገ ያለውን ያላሰለሰ ጥረት ዘርዝረዋል።
ለሀገሪቱ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም እንዲሁ አስረድተዋል።
አየርላንድ እነዚህ በኢትዮጵያ መንግስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እና በሀገሪቱ እየተካሄዱ ያሉትን የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መደገፍ ነበረባት ነው ያሉት።
ነገር ግን ዓየርላንድ አባል በሆነችባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እና የአውሮፓ ህብረትን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጥቃቷን ቀጥላለች ብለዋል።
ዓየርላንድ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ላይ እየፈፀመች ካለችው ጥቃት እንድትታቀብ ኢትዮጵያ ያቀረበችውንም ጥሪ ከቁብ ሳትቆጥር መቅረቷንም ነው ያስገነዘቡት።
በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት ግንኙነት መሻሻል ላይም ዓየርላንድ እክል መፍጠሯንም አቶ ደመቀ በደብዳቤው ላይ አንስተዋል።
በመሆኑም ሀገሪቱ ከዚህ ኢትዮጵያን ከማጥቃት ድርጊቷ ልትታቀብ ይግባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ለማደስ ፍላጎት አላት ያሉት አቶ ደመቀ፥ ዓየርላንድ በኢትዮጵያ ልክ ለግንኙነቱ መሻሻል ፍላጎት እንዳለት ግን አናውቅም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ግንኙነቱን ለማሻሻል ያደረገቻቸው ሙከራዎች ሁሉ መክሸፋቸውንም አንስተዋል።
በተቃራኒው ዓየርላንድ ህወሓትን በመደገፍ በፀጥታው ምክር ቤት ያላትን መቀመጫ በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር ግፊት እያደረገች መሆኗን ነው ያስረዱት።
በመሆኑም ዓየርላንድ ከዚህ ኢትዮጵያን የማጥቃት ድርጊቷ እንድትታቀብ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጠይቀዋል።