አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2015 (ኤፍ ቢሲ) በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በደረሰ የድልድይ መፍረስ አደጋ የተጎዱ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች በሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ዛሬ ጠዋት ላይ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚፈተኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲውን ሁለት ካምፓሶች የሚያገናኘው ድልድይ በመፍረሱ ድልድዩን ሲሻገሩ በነበሩ የተወሰኑ ተማሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሁኔታቸውንም መላው የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና የትምህርት ሚኒስቴር ግብረሀይል በቅርበት እየተከታተሉት የሚገኝ ሲሆን ወላጆች እንዳይደናገጡ ሚኒስቴሩ ጠይቋል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በቀጣይ በሚሰጠው ፈተና የሚፈተኑ መሆኑን እና ሌሎች ተማሪዎች በአጋጣሚው ሳይረበሹ ተረጋግተው እንዲፈተኑም ሚኒስቴሩ ጠይቋል፡፡
የሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሳ በበኩላቸው አደጋው የተከሰተው ጠዋት አንድ ሰዓት ከመጠን በላይ የሆኑ ተማሪዎች በድልድዩ ላይ በመውጣታቸው ድልድዩ ከሚሸከመው አቅም ላይ በሆነ ሁኔታ የተከሰተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአደጋውው ውስን ተማሪዎች የመቁሰል አደጋዎች የደረሰባቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ምንም አይነት የሞት አደጋ አልተከሰተም ያሉት ሀላፊው ተማሪዎቹም በፍጥነት ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉንም ነው የተናገሩት፡፡
በተከሰተው ድንገተና አደጋ ተደናግጠው ከግቢው የወጡ ተማሪዎችም በጊዜ ተመልሰው ፈተናውን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተለያየ መልኩ ጉዳዩን አጋነው በማውራት ሰው እንዳይረጋጋ ከሚያደርጉ ችግሮች ህዝቡ እራሱን መጠበቅ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በብርሃኑ በጋሻው