ስፓርት

በሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ደቡብ ሱዳን ወደ ግማሽ ፍጻሜ አለፈች

By Shambel Mihret

October 09, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት (ሴካፋ) ደቡብ ሱዳን ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፏን አረጋግጣለች።

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እየተከናወነ የሚገኘውና ሰባተኛ ቀኑን በያዘው ውድድር ÷ ዛሬ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ተካሄደዋል።

በምድብ ሁለት ደቡብ ሱዳንና ብሩንዲ ያደረጉት ጨዋታ 1 ለ 1 ተጠናቋል።

ውጤቱንም ተከትሎ ደቡብ ሱዳን ከምድቧ ዩጋንዳን ተከትላ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፋለች።

በምድብ አንድ በተደረገው ጨዋታ ታንዛኒያ ሶማሊያን 2 ለ 1 ስታሸንፍ÷በዚሁ ምድብ ሁለቱ አገራት ቀድመው ለግማሽ ፍጻሜ ማለፋቸው ይታወቃል።

በምድብ ሁለት አስተናጋጅ ሀገር ኢትዮጵያ ሁለት ጨዋታ ተሸንፋ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አልቻለችም።

በግማሽ ፍጻሜው ዩጋንዳ ከሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን ከታንዛንያ ጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሴካፋ የእግር ኳስ ውድድር እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ይቆያል።

በውድድሩ አንደኛ እና ሁለተኛ የሚወጡ ሀገራት በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ዞኑን ወክለው ይሳተፋሉ።