አዲስ አበባ፣መስከረም 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ጋና ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጊዜ ጀምሮ ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው የኢፌዴሪ የማዕድን ሚኒስትር – ታከለ ኡማ ገለፁ።
በጋና ኤምባሲ በተዘጋጀው የኢትዮ-ጋና የወዳጅነት ምሽት በክብር እንግድነት የተገኙት የማዕድን ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ከጋና ጋር የአፍሪካ ህብረት እንዲቋቋም ባስቻለው የፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ መነሻነት የበለጠ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ከመጠናከሩም በላይ በአፍሪካዊ ጉዳዮች ላይ በቅርበት እና በጋራ ለመስራት ያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለአፍሪካ ሀገራት ነጻነት እና ለአፍሪካ ህብረት መጠናከር ጉልህ አስተዋጾኦ ማበርከታቸውን የገለጹት በኢትዮጵያ የጋና ኢምባሲ አምባሳደር አሟ ቹም፥ ሀገራቱ በአፍሪካ አህጉር ነጻ እና የተረጋጋ የመንግስት ስርዓት ካላቸው ሀገራት መካከል በቀዳሚነት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
ጋና ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በተፈጥሮ የማዕድን ሀብት ባለቤት መሆኗ የሚታወቅ ነው ያሉት አምባሳደሯ፥ በጤና ስርዓት፣ በኢኮኖሚ ዕድገት እና በሰብዓዊ ልማት ላይ ጠንካራ ውጤቶችን እያስመዘገበች ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊና የብሔራዊ ኮሚቴው ፀሐፊ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው፥ ቀደምት የኢትዮጵያ መሪዎች ቀዳማዊ አጼ ሃይለስላሴና የጋና ፕሬዚዳንት ኩዋሚ ንኩርማ ለፓን አፍሪካዊነት ንቅናቄና ለአፍሪካዊያን ተቋማት ግንባታ እውን መሆን የመሪነት ሚና እንደነበራቸው ገልፀዋል።
ታሪካዊና ፖለቲካዊ የኢትዮ-ጋና ግንኙነት በጸረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄና በአፍሪካዊ ወንድማማችነት ጉዳዮች ድል ያስመዘገቡና ለሌሎች ተምሳሌት የሆነ ግንኙነት አላቸውም ብለዋል፡፡