ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሳዑዲ ዓረቢያ ወደ አሜሪካ በምትልከው የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ አደረገች

By Tamrat Bishaw

October 07, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳዑዲ ዓረቢያ ወደ አሜሪካ በምትልከው የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጓ ተገልጿል፡፡

በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኘው ሳዑዲ አራምኮ በህዳር ወር ወደ አሜሪካ በሚልከው ድፍድፍ ነዳጅ መሸጫ ዋጋ ላይ የ20 ሳንቲም ጭማሪ ማድረጉን አስታውቋል።

ይሁን እንጅ ዋነኛ የገበያ መዳረሻው በሆነው እስያ ገበያ ምንም ጭማሪ አለማድረጉን ብሉምበርግ አስነብቧል።

ለሰሜን ምዕራብ አውሮፓ እና ለሜዲትራኒያን አካባቢ የድፍድፍ ነዳጅ መሸጫ ዋጋ ቀንሷል ነው የተባለው።

የነዳጅ አምራች እና ላኪ ሀገራት ድርጅት (ኦፔክ) ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ የምርት መጠኑን በቀን በ2 ሚሊየን በርሜል ለመቀነስ መወሰኑ የዓለም የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋን የበለጠ እንደሚያባብሰው ዘገባው ጠቁሟል።

አሜሪካ የኃይል ዋጋ ማሻቀብን ተከትሎ ሀገራት ቁጣቸውን እየገለጹ ባለበት በዚህ ወቅት ምርት ለመቀነስ መወሰን አርቆ አለማየት ነው ስትል ተችታለች፡፡

ሩሲያ ከዩክሬን ግጭት ጋር በተያያዘ በተጣለባት ማዕቀብ የተነሳ ከሰኔ ወር ጀምሮ የዓለም አቀፉ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ መቀነሱ ተገልጿል፡፡

ይሁንና በበርሜል 90 ዶላር የሚጠጋው አሁን ያለው ዋጋ ግን በዚህ አመት ወደ 20 በመቶ ከፍ ማለቱ ተገልጿል፡፡

ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚታየው የዋጋ ግሽበት አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ የአር ቲ ዘገባ ያመላክታል።