አዲስ አበባ፣ መስከረም 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ስቴፋን ጆቢን ጋር በሁለቱ ሀገራት የጋራ ግንኙነት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ኢትዮጵያ የፖለቲካና መሠል ልዩነቶችን በሰከነ መንገድ በውይይትና በንግግር ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁማ እየሰራች መሆኑን አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ካናዳ የፌዴራል ስርዓት ተከታይ ሀገራት እንደ መሆናቸው በብዝሃነት አያያዝ፣ በፊስካል ሽግግር ስርዓት እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ከካናዳ መልካም ልምዶችን ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗንም ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም የካናዳ መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር አፈጉባዔው አድንቀዋል፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤት ከካናዳ አቻ ምክር ቤት ጋር በትብብር ለመሥራት ያለውን ፅኑ ፍላጎትም ገልፀዋል።
ስቴፋን ጆቢን በበኩላቸው÷ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በማሕባራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ለረዥም ጊዜ ተጠናክሮ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡
አምባሳደሩ የካናዳ መንግስት የኢትዮጵያን ልማት ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
ኢትዮጵያና ካናዳ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው መገለጹንም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!