Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ዩኒቨርሲቲዎች ያደረጉት ዝግጅት አስደሳች ነው-ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ዩኒቨርሲቲዎች ያደረጉት ዝግጅት አስደሳች መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃነ ነጋ ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሩ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ለመስጠት ያደረገውን ዝግጅት ጎብኝተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ÷የጉብኝቱ ዓላማ ፈተናውን በደህንነት፣ያለምንም የፈተና ስርቆትና ኩረጃ ለማካሄድ  የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን መመልከት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ  ቆይታቸው ማደሪያዎቻቸውና መመገቢያቸው የተስተካከለ እንዲሆን እንደወላጅ ሀላፊነት ወስደን እየሰራን ነው  ብለዋል።

እስካሁን እየታየ ያለው ውጤትም  አስደሳች መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ ዩኒቨርሲቲዎችና የተለያዩ የመንግስት ተቋማት እያደረጉት ያለው ጥረቶች ምን ያህል አቅም እንዳለ የሚያሳይና የሚያስመሰግን  መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ከጸጥታ  ችግር ጋር በተያያዘ አሁን መፈተን ለማይችሉ ተማሪዎች ፈተናውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

አሁን የሚሰጠው ፈተና የ2014ዓ.ም ትምህርት ዘመን መሆኑን በማንሳት  በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናም በግንቦት ወር  እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

Exit mobile version