አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የነዳጅ አምራችና ላኪ ሀገራት (ኦፔክ) የነዳጅ ምርትን ለመቀነስ መስማማታቸው ተሰምቷል፡፡
ሀገራቱ አሁን ላይ ያለው የነዳጅ አቅርቦት ቀውስ መፍትሄ ሳያገኝ በቀን የሚያመርቱትን ነዳጅ በ2 ሚሊየን በርሜል ለመቀነስ ተስማምተናል ብለዋል፡፡
ይህም ከዓለም አቀፉ አቅርቦት 2 በመቶ ያክል እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
አምራች እና ላኪ ሀገራቱ የተስማሙበት የምርት ቅነሳ ከፈረንጆቹ 2020 ወዲህ እጅግ ከፍተኛው መሆኑም ነው የተገለጸው።
ይህ የምርት ቅነሳም ከመጪው የፈረንጆቹ ህዳር ወር ጀምሮ እንደሚተገበር አር ቲ በዘገባው አስታወሷል።
ከነዳጅ ጋር በተያያዘ ሩሲያ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓውያኑ ሀገራት “ነዳጅን ሀገራትን ለማንበርከክ እየተጠቀመችበት” ነው በሚል ስትወነጀል ቆይታለች።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የነዳጅ ምርት ባለበት እንዲቀጥል ወይም ከፍ እንዲል ቢወተውቱም ፍላጎታቸውን ግን ተፈጻሚ ማድረግ አልቻሉም።
የባይደን አስተዳደር የምርት ቅነሳውን “ጠብ አጫሪነት” ነው ሲል ቢገልጸውም ሀገራቱን ግን ከውሳኔ አላገዳቸውም።
የኦፔክ አባል ሀገራት የኢነርጂ ሚኒስትሮች ደግሞ የምርት ቅነሳው ፖለቲካዊ አንድምታን ያዘለ ሳይሆን “የኢኮኖሚ ድቀትን” በመፍራት የተወሰነ ውሳኔ መሆኑን ይገልጻሉ።