አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በወላይታ ዞን በሶዶ ዙሪያ ወረዳ ከ20 ዓመታት በላይ ተዘግቶ የቆየው አባባ ብሩ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ሰሜን አሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ፡፡
በገንዘብ እጥረትና በሌሎች ምክንያቶች ለዓመታት አገልግሎት መስጠት ያቆመው አባባ ብሩ 1ኛ ደረጃ የሕዝብ ትምህርት ቤት÷ የተከፈተው በ1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነበር፡፡
የትምህርት ቤቱ መዘጋት የቆጫቸው በአሜሪካ እና በካናዳ የሚኖሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት ÷ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመማሪያ ክፍሎችን በማደስ ፣ ወንበሮችን በማሟላት፣ የመፀዳጃ ቤት በመገንባት እንዲሁም ለ180 ተማሪዎች የደንብ ልብስ በማዘጋጀት፣ ጫማ፣ ቦርሳ፣ ደብተርና እስክርቢቶ በማሟላት ትምህርት ቤቱ ዳግም እንዲከፈት አድርገዋል፡፡
ትምህርት ቤቱ በትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ መሰረት መስፈርቶችን ማሟላቱ ተገልጿል፡፡
ነገ ሀገር ተረካቢ በስነ ምግባር የታነፁ ዜጎችን ለማፍራት እንዲቻል ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉና ትምርት ቤቱን እስከ 2ኛ ደረጃ የማስፋት ዕቅድ እንዳላቸው ድጋፍ አድራጊዎቹ ተናግረዋል፡፡
ልጆቻቸውን ለትምህርት ሩቅ ቦታ ይልኩ የነበሩ ወላጆችም በትምህርት ቤቱ ዳግም አገልግሎት መስጠት መደሰታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በኡሱማን መሀመድ