አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዕድል እና አማራጮችን የሚያስተዋውቅ መድረክ በጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ ተካሄደ።
መድረኩ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው “ዎዳ የግል ኢንዱስትሪ ፓርክ” በጥምረት ነው።
በመድረኩ በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በህትመት ፣ በፋርማሲቲካል ፣ በኃይል፣ በኤሌክትሮኒክስ እና ፋይናንስ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ የጃፓን እና ዓለም አቀፍ ባለሐብቶች የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ሰፊ ገለጻ ተሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳ፥ በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት ማበራታቸዎች፣ ስለተደረጉ የፖሊሲ ለውጦች እና ማሻሻያዎች እንዲሁም ምቹ የኢንቨስትመንት ካባቢ እና የተሳለጠ የኢንቨትመንት አሠራር ለባለሐብቶቹ አብራርተዋል፡፡
ከመድረኩ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ካሳዩ ባለሐብቶች ጋርም የአንድ ለአንድ ውይይትና ጉብኝት ተካሂዷል፡፡
በተጨማሪም የልዑክ ቡድኑ ከጃፓኑ የኢንቨትመንት እና ቢዝነስ ፕሮሞሽን ተቋም ጄትሮ (JETRO) ጋር በጋራ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዕድል እና አማራጮች ለማስተዋወቅ እና የጃፓን ባለሐብቶችን ወደ ኢትዮጵያ በመጋበዝ የኢንቨትመንት ከባቢውን እንዲመለከቱ የማድረግ ሥራ ማከናወን በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መምከራቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ አመላክቷል፡፡