አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዕምሮ ህመም በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ማህበራዊ ቀውስ፣ ተፈጥሯዊ አደጋ፣ ጦርነት፣ የኑሮ ውድነት እና ወረርሽኝ ለአዕምሮ ህመም መከሰት ዋነኛ መንገዶች እንደሚሆኑ የስነ ልቦና ህክምና ባለሙያዋ ቤቴል አብርሃም አብራርተዋል፡፡
እነዚህ ቀውሶች ተዳምረው ሰው ህይወቱን ባሰበው መንገድ እንዳይመራ እና ነገን እንዳያይ ያደርጋሉ የሚሉት ባለሙያዋ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ውጥረት እንደሚፈጠርም አንስተዋል፡፡
በጊዜው እርዳታ ያላገኘ እና ያልታከመ ውጥረት ለተለያየ የአዕምሮ ህመም ችግር እንደሚዳርግም ባለሙያዋ ይገልፃሉ፡፡
የአዕምሮ ህመም ችግር ሲፈጠር ብዙዎች እንደማይድ በማሰብ ታማሚውን የመሸሽ እና የማግለል አዝማሚያ እንደሚያሳዩ የሚገልፁት በአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተቀናጀ የአዕምሮ ጤና ህክምና ስፔሻሊስት አበበ አምባው ናቸው።
እንደ እርሳቸው ገለጻ ታማሚው አስፈላጊው ድጋፍና እንክብካቤ ቢደረግለት ሊሻለው ይችላል።
የአዕምሮ ጤና ችግርን ከእርግማን፣ ከክፉ መንፈስ አሰራር እንዲሁም የግለሰቡ ደካማነትና ስንፍና እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች እንዳሉ የሚናገሩት የስነ ልቦና ህክምና ባለሙያዋ ቤቴል አብርሃም ነገር ግን ይህ ትክክል እንዳልሆነ ነው የሚገልጹት።
የአዕምሮ ህመም አይድንም፣ ህክምና የለውም የሚሉ አመለካከቶች ደግሞ በአዕምሮ የጤና ችግር ዙሪያ የሚስተዋሉ ሌላው የግንዛቤ እጥረት ችግሮች እንደሆኑም ያነሳሉ፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ በአዕምሮ ጤና ችግር ዙሪያ የተሳሳቱ አመለካከቶችና የግንዛቤ ክፍተቶች በስፋት ስለመኖራቸው የሚገልፁት የአዕምሮ ጤና ህክምና ስፔሻሊስቱ አበበ አምባው፥ በዚህ የተነሳ በችግሩ ዙሪያ በያገባኛል ስሜት የሚንቀሳቀሱ ጥቂቶች ብቻ እንዲሆኑ አድርጓል ነው የሚሉት።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ከተዛቡ መሰል አመለካከቶች በመላቀቅ በያገባኛል ስሜት ሊንቀሳቀስና ታማሚዎችን ሊደግፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የአዕምሮ ጤና ችግር ያጋጠማቸው ህሙማንን ወደ ህክምና በመውሰድም ተገቢውን እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያዎቹ ምክረ ሀሳባቸውን ለግሰዋል፡፡
በነገሮች አብዝቶ አለመጨነቅ፣ ለመዝናናት እና ከጭንቀት ነጻ ለመሆን ለራስ ጊዜ መስጠት፣ በቂ እረፍት ማድረግንም የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ።