አዲስ አበባ ፣ መስከረም 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካውያን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ለአህጉሪቱ እድገት እና ብልፅግና በማዋል ረገድ እንዲተባበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ያለውን የፓን አፍሪካ ኢንተለጀንስ ኮንፈረንስን በንግግር ከፍተዋል።
በዚሁ ንግግራቸው አሁን ላይ ሳይንስ የየዕለት እንቅስቃሴ መሠረት መሆኑን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ አዘጋጅታ በመተግበር በአብዮት ውስጥ መሆኗን ነው የተናገሩት።
በተለይም የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቴክኖሎጂውን በግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት እና መንግስት አስተዳደር ዘርፎች በመጠቀም እመርታ እያስመዘገበ መሆኑን ገልፀዋል።
ዛሬ የተከፈተውም የሳይንስ ሙዚየም በዘርፉ ወጣቶችን የፈጠራ አቅም እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ ሲሆን፥ ዛሬ ተመርቆ በተከፈተው የሳይንስ ሙዚየም ነው እየተካሄደ ይገኛል።
ኮንፈረንሱ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አፍሪካን ማብቃት በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው።
በሁለት ቀናት ቆይታው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ልማት የሚገኝበትን ደረጃ እና ለአህጉሪቱ ልማት ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋፅዖ የተመለከቱ ሳይንሳዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም በዘርፉ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ልምድ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ነው የተባለው።