የሀገር ውስጥ ዜና

“ስለ ኢትዮጵያ” የፓናል ውይይት በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው

By Mikias Ayele

October 04, 2022

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 11ኛው “ስለ ኢትዮጵያ” የፓናል ውይይት በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የፓናል ውይይቱ “አሸናፊ ሕዝብ ስለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።

በውይይቱ ላይ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሃመድ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እና ረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በመድረኩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ዘሀራ ሁመድ፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ አትሌቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የፈጠራ ባለሙያዎች እና ሌሎች እንግዶች ተሳታፊዎች ናቸው።

ከመድረኩ ቀደም ብሎ “ስለ ኢትዮጵያ” የተሰኘ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ ተከፍቷል፡፡

አውደ ርዕዩን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አይሻ መሀመድና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ መርቀው ከፍተውታል።

በአውደ ርዕዩ ከ1960ዎቹ ጀምሮ እስከ አሁን በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተከሰቱ አበይት ኩነቶችን የሚያስቃኙ ፎቶ ግራፎች ለዕይታ ቀርበዋል።

በተለይም ኢትዮጵያውያን በኅልውና ዘመቻው ያሳዩት ተጋድሎና ሀገርን ለማዳን የተከፈሉ መስዋዕትነቶችን የሚያሳዩ ፎቶ ግራፎች ለዕይታ ቀርበዋል፡፡