አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አትሌት ታዬ ግርማ የተከለከለ የስፖርት አበረታች ቅመም በመጠቀሙ ለ5 ዓመት ከ4 ወር ከማንኛውም የስፖርት ውድድር መታገዱን የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን አስታወቀ።
ከመጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ አትሌቱ ያስመዘገባቸው ውጤቶች እንዲሰረዙና በውድድሮቹ ያገኛቸው ሽልማቶች ተመላሽ እንዲሆኑ ውሳኔ ማስተላለፉን ባለስልጣኑ አመላክቷል።
መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው 50ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ እንዲሁም ሰኔ 13 ቀን 2013 ዓ.ም በጣሊያን ቴሌሴ ቴርሜ ከተማ በተከናወነው የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ላይ በተደረገው የአበረታች ቅመሞች ምርመራ አትሌት ታዬ ግርማ ‘Erythropoietin’ የተሰኘ የተከለከለ አበረታች ቅመም ሁለት ጊዜ መጠቀሙን የሚያመላክት ውጤት ማግኘት መቻሉን አመላክቷል።
ባለስልጣኑ ውጤቱን ተመርኩዞ በአትሌት ታዬ ላይ ጊዜያዊ እገዳ በመጣል ባካሄደው ምርምራ አትሌቱ ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቶታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተጨማሪም አትሌት ታዬ ከመጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ያስመዘገባቸው ውጤቶች እንዲሰረዙ እና በውድድሮቹ ያገኛቸው ሽልማቶች ተመላሽ እንዲሆኑ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡
የሚመለከታቸው አካላትም አትሌቱ ቅጣቱን ጨርሶ እገዳው እስከሚነሳለት ድረስ በማንኛውም ውድድር ላይ እንዳይሳተፍና የቅጣቱ ተፈጻሚነት ላይ ክትትል እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!