አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት በፍፁም ሠላማዊ ሁኔታ መጠናቀቃቸው የህዝቡን ጠንካራ የሠላም ዘብነት ያሳየ ነው ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ በመስከረም ወር ኢትዮጵያ አምራ የታየችባቸው ህዝባዊ እና ኃይማኖታዊ በዓላት በድምቀትና በሰከነ ሁኔታ መከበራቸውን ገልጿል፡፡
የአዲስ አመት አቀባበል ከዋዜማው ጀምሮ፤ የመስቀል በዓል፣ ኢሬቻ እና የግሸን ደብረ ከርቤ በዓላት፣ በደቡባዊ ኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎችና ዞኖች የተከበሩ በዓላትም ጭምር ያለምንም የፀጥታ ችግር በሚሊዮኖች በሚቆጠር ህዝብና በርካታ ቱሪስቶች ተሳትፈውባቸው ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቀውና በታላላቅ ፈጠራ ታጅበው በድምቀት መከበራቸውንም አውስቷል፡፡
ለበዓላቱ በድምቀት መከበር መላው ህዝብ እንደወትሮው ሁሉ የላቀ አስተዋፅዖ አበርክቷል፤ ለዚህም ከፍ ያለ ምስጋና ይገባዋል ነው ያለው አገልግሎቱ።
በዓላቱን ለማክበር ወደተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተጓዙ ወገኖቹን ህዝቡ በፍፁም ኢትዮጵያዊ ፍቅር ተቀብሎ ማስተናገዱም ተመላክቷል፡፡
የፌደራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎችም ከህዝቡ ጋር በብቃት ያከናወኑት የሰላምና የደኅንነት ሥራ፤ በዓላቱን ተጠቅመው ጥፋት አስበው የነበሩ የሽብር ቡድኖች እቅድ እንዲከሽፍ አድርጓል፡፡
የሚዲያ ተቋማትም የበዓላቱን ድምቀት በማስተጋባት ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር፣ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምና የስራ ፈጠራ እንዲስፋፋ ከፍተኛ የማነቃቃት ሥራ ሠርተዋል ነው ያለው፡፡
የወርሃ መስከረም በዓላት በድምቀትና በፍጹም ሰላም ተከብረው መጠናቀቃቸው ሀገራችን በፈተና ውስጥም ሆና ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን እንደምትችል ያረጋገጠና የኢትዮጵያውያንንም የአብሮነት እሴት ዳግም በተግባር ያስመሰከረ መሆኑን በመግለጫው ተገልጿል፡፡
በዓላቱ በሰላም እና በድምቀት እንዲከበሩ አስተዋፅዖ ላበረከተው መላው ህዝብ፣ በየደረጃው ያሉ የፀጥታ አካላት እና የመንግስት መዋቅሮች፣ ለኃይማኖት አባቶች፣ ለሀገር ሽማግሌዎች፣ ለወጣቶችና ለሚዲያ ተቋማት በሙሉ መንግሥት ከፍ ያለ ምስጋና እንደሚያቀርብ ነው ያስታወቀው፡፡