አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጀመሪያው ዙር አሸናፊው ያልተለየበት የብራዚል ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወደ ሁለተኛ ዙር መሸጋገሩን የሀገሪቱ ምርጫ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በብራዚል 11 ዕጩዎች የተሳተፉበት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በትናንትናው ዕለት ተካሂዷል፡፡
በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ምርጫም ቀኝ ዘመሙ እና የአሁኑ ፕሬዚዳንት ጃየር ቦልሶናሮ 43 ነጥብ 5 በመቶ ድምጽ ማግኘት መቻላቸው ተገልጿል፡፡
የጃየር ቦልሶናሮ ዋነኛ ተቀናቀኝ እና ግራ ዘመሙ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በበኩላቸው 48 ነጥብ 1 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን አርቲ ዘግቧል፡፡
ይሁን እንጂ የመጀመሪያውን ዙር ምርጫ በበላይነት ያጠናቀቁት ሉላ ዳ ሲልቫ ከ50 በመቶ ድምጽ በላይ ማግኘት ባለመቻላቸው አሸናፊ መሆን አልቻሉም ተብሏል፡፡
በብራዚል ምርጫ ህግ አንድ ተፎካካሪ በመጀመሪያ ዙር አሸናፊ ለመሆን 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ድምጽ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡
ይህን ተከትሎም የብራዚልን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊን ለመለየት ምርጫው ወደ ሁለተኛ ዙር መሸጋገሩን የሀገሪቱ ምርጫ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በፈረንጆቹ ጥቅምት 30 በሚካሄደው ሁለተኛው ዙር ምርጫም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ እና በስልጣን ላይ ሚገኙት ጃየር ቦልሶናሮ የሚፋለሙ ይሆናል፡፡