አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጢስ ዓባይ 2 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ በ2015 በጀት ዓመት 220 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ማቀዱን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ደጀኔ ጉታ ተናገሩ፡፡
ዕቅዱን ለማሳካትና የኦፕሬሽን ሥራውን አስተማማኝ ለማድረግ መደበኛና ድንገተኛ የጥገና ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም አቶ ደጀኔ ገልጸዋል፡፡
በክረምቱ ወራት የሚፈጠረውን ከፍተኛ ውኃ በመጠቀም ተርባይኖቹ በሙሉ አቅማቸው እንዲሠሩ በመደረጉ ያለፉት ሁለት ወራት አፈፃፀምም የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ማሳካት እንደሚቻል አመላክተዋል ብለዋል፡፡
የጣቢያው ዩኒቶች በተደረገላቸው ጥገና ተርባይኖቹ በሙሉ አቅማቸው ኃይል እያመነጩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በገበያ ላይ በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉና ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጡ የመለዋወጫ ዕቃዎችን በሌላ የመተካት (የሞዲፊኬሽን) ሥራ በመሥራት ተቋሙን ከወጪ ለመታደግ መታቀዱን የኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመላክታል፡፡
በቮልቴጅ መቆጣጠሪያ (ኤግዛይቴሽን ሲስተም)፣ የተርባይን ፍሪኩዌንሲ መቆጣጠሪያ (ገቨርነር ሲስተም) እና ኮንትሮሊንግ ሲስተሙ ላይ የጥገና ሥራዎችን ለመሥራት መታቀዱም ተጠቁሟል፡፡
የጢስ ዓባይ ማመንጫ ጣቢያ ባለፈው በጀት ዓመት 157 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማመንጨት አቅዶ÷ 182 ነጥብ 3 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨቱ ይታወሳል፡፡