የሀገር ውስጥ ዜና

ከንቲባ አዳነች የመዲናዋ ነዋሪ ከዘመን መለወጫ ጀምሮ ያሉት በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ላደረገው አስተዋፅኦ ምስጋና አቀረቡ

By Feven Bishaw

October 01, 2022

 

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመዲናዋ ነዋሪ ከዘመን መለወጫ ጀምሮ የተከናወኑት በዓላት በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ ላደረገው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስጋና አቀረቡ፡፡

ከንቲባዋ የአዲስ አበባ ህዝብ ከዘመን መለወጫ በዓል ጀምሮ ተደራራቢ ኃላፊነቶችን በሚገባ በመወጣት እኩይ ኃይሎችን አሳፍሯቸዋል ብለዋል፡፡

ይህንን ታላቅ ህዝብ፣ ይህንን ጨዋ ህዝብ ደግመን ደጋግመን እናመሰግነዋለን ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ከለውጡ ወዲህ ለ4ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የተከበረው ሆረ ፊንፊኔ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ከአዲስ አበባ ፣ ከኦሮሚያ ፣ ከሌሎች ክልሎችና ከውጪ ሀገራት ጭምር የተሳተፈበት እንደሆነ ከንቲባ አዳነች በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል፡፡

በዓሉ “ኢትዮጵያውያን በተለያየ መንገድ ተከፋፈሉ፥ ተራራቁ” እየተባለ የሚነገረውንም አሉባልታ ያፈረሰና የህዝቦች አንድነትና ትብብር የበለጠነ ጎልቶ በወጣበት ደረጃ ከፍ ብሎ መከበሩንም ጠቅሰዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኖች በጦር ሜዳ የደረሰባቸውን ኪሳራ ለማካካስና እሴቱንም ለማሳነስ ሙከራ ማድረጋቸውን አንስተው፥ ነገር ግን ሰላም ወዳዱ የአዲስ አበባ ህዝብ፣ እንዳይሳካላቸው የአንበሳውን ድርሻ መወጣቱን ተናግረዋል፡፡

የኢሬቻ በዓል ፈጣሪ የሚመሰገንበት በዓል እንጂ የሌላ ፖለቲካ ፍላጎት ማሳኪያ እንዳይሆን ህዝቡ ታግሏል፤ እድል እንዳያገኙም የጥፋት መንገዶችን ሁሉ ዝግ አድርጎባቸዋል ብለዋል፡፡

በፀጥታ ኃይሎች በተለይም የፖሊስ ኃይልና ህዝባዊ ሰራዊታችን ደንብ በማስከበር ረገድ በተባበረ መንገድ ከህዝቡ ጋር ሰርተው ውጤታማ ማድረግ ችለዋል ነው ያሉት ከንቲባዋ፡፡

ከንቲባዋ አዳነች እንዳሉት፥ “የኢሬቻ በዓል ገና አላለቀም፤ ህዝቡ የሆረ ሀርሴዴ በዓልን ለማክበር ወደ ቢሾፍቱ እየሄደ ነው ፤ ተመልሶ የሚያድረውም አዲስ አበባ ላይ ነው፤ ነገም በተመሳሳይ ሁኔታ ህዝቡ በሰላም ወደመጣበት እስኪመለስ ድረስ አሁን የታየው ርብርብና አብሮነት ሊቀጥል ይገባል።

የሚድያ ተቋማትን በሚመለከትም “የበዓሉን ትክክለኛ ገፅታ ለዓለም ለማስተዋወቅ በመቻላቸው ሁሉንም ከልቤ አመሰግናለሁ”ማለታቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡