አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ አራት የዩክሬን ግዛቶችን በይፋ ወደ ግዛቷ ለማዋሃድ የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራረመች።
ስምምነቱን የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሉሃንስክ፣ ዶኔስክ፣ ኬርሰን እና ዛፖሮዢየ አስተዳዳሪዎች ጋር በዛሬው እለት ተፈራርመውታል።
20 በመቶ የዩክሬን ክፍል ይሸፍናሉ የሚባሉት አራቱ ግዛቶች ባለፉት ቀናት ከሩሲያ ጋር ለመዋሃድ ህዝበ ውሳኔ ማካሄዳቸው ይታወሳል።
የህዝበ ውሳኔው ውጤት ረቡዕ ይፋ ሲሆን፥ በአማካይ ከ94 በመቶ በላይ የየግዛቶቹ ነዋሪዎች ሩሲያን ለመዋሃድ መወሰናቸው ተገልጿል።
የዛሬውን ስምምነት ፀድቆ ግዛቶቹ በይፋ የሩሲያ አካል ይሆኑ ዘንድም የህገ መንግስታዊው ፍርድ ቤት እና የሩሲያን ፓርላማ (ዱማ) ይሁንታን ማግኘት ይኖርበታል።
ፍርድ ቤቱ ስምምነቱ የሩሲያን ህግ የተከተለ ነው በሚል ከገመገመውና ካጣራ በኋላ ለምክር ቤቱ የሚመራው ይሆናል።
ይህን ሂደት ካለፈ በኋላም ለፌደራሉ ወይም በላይኛው ምክር ቤት ቀርቦ ይሁንታን ካገኘ ግዛቶቹ የሩሲያ አንድ አካል ሆነው እንደሚቀጥሉ አር ቲ ዘግቧል።
የፍርድ ቤቱ እና ምክር ቤቱ አባላትም በጉዳዩ ላይ ለመወሰን ከሶስት ቀናት በኋላ ይሰየማሉ ተብሏል።