አዲስ አበባ ፣ መስከረም 20 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢሬቻ የገዳ ሥርዓት ፍልስፍና ነጸብራቅ የወንድማማችነት፣ የዕርቅና የይቅርታ በዓል ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ ገለጹ።
አቶ ፈቃዱ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም የኦሮሞ ህዝብ ሰላምን፣ እርቅን፣ ፍቅርን እና ወንድማማችነትን የሚገነቡ እና እውነተኛ አብሮ መኖርን የሚያጎለብቱ ባህሎች ባለቤት መሆኑን ጠቅሰው፥ የኢሬቻ በዓል የህዝቡ ባህላዊ ነጸብራቅ እንደሆነም አንስተዋል።
የኢሬቻ በዓል የመከባበር፣ የእርቅና የምስጋና በዓል የሀገሪቱ ህዝቦች የሚሳተፉበትና በደስታ የሚጠባበቁበት ሆኗልም ነው ያሉት።
ኢሬቻ የገዳ ስርዓት ነጸብራቅ እና የኦሮሞ ህዝብ ለዓለም ያበረከተው ልዩ ስጦታ መሆኑን በመጥቀስ፥ ኢሬቻ የምስጋና በዓል መሆኑንም ገልጸዋል።
ሰላም፣ እርቅ፣ ፍቅር፣ ወንድማማችነት እና አንድነት የኢሬቻ ዋና መገለጫዎች ናቸው ያሉት አቶ ፈቃዱ፥ ኢሬቻ የብርሃን ምልክት፣ አስታራቂ፣ አብሮ የመኖር መገለጫ እና የአንድነት ምልክት መሆኑንም አመላክተዋል።
ኢሬቻ የምስጋና ቀን፣ የአንድነትና የዕርቅ ምልክት መሆኑን ያነሱት ሃላፊው፥ የብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች መሰባሰቢያ እንዲሁም የዓለም ሃብት እየሆነ መጥቷልም ነው ያሉት።
የኢሬቻን በዓል ስናከብር የበዓሉን ወጎችና መገለጫዎች የበለጠ በማጠናከርና ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ ሊሆን እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
የበዓሉን እውነታዎች፣ የአንድነትና የወንድማማችነት መገለጫዎች ከበዓሉ አከባበር በዘለለ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ መተግበር እንደሚገባም አውስተዋል።
አያይዘውም ኢሬቻ የበረከት እና የፍቅር ቦታ ነውና የዚህ የተቀደሰ ሥነ ሥርዓት ተሳታፊዎች አንድነትንና ወንድማማችነትን በማጎልበት፣ ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ ኢሬቻን የወንድማማችነትና የአንድነት መድረክ ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል የደስታ፣ የሰላምና የአንድነት እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።