አዲስ አበባ ፣ መስከረም 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ሕጻናት ለድምፅ ትዕዛዝ ምላሽ የሚሰጡ ሰው ሰራሽ አስተውሎ ያላቸው መሣሪያዎችን ለረጅም ጊዜ ከመጠቀማቸው የተነሳ ስሜታቸው እና በጥልቀት የመረዳት አቅማቸው እንደሚጎዳ ጥናት አመላከተ፡፡
አናንያ እና አንሞል አሮራ የተሰኙት የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ÷በግብዓትነት “ጉግል ሆም”፣ “አማዞን አሌክሳ”፣ እና “አፕል ሲሪ” የተሰኙትን ለድምፅ ትዕዛዝ ምላሽ የሚሰጡ ሰው ሰራሽ አስተውሎ ያላቸው የተግባቦት ቁሶችን ተጠቅመዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣው የሰው ሰራሽ አስተውሎ ተግባቦት ቁሶች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ መሣሪያዎቹ በሰው ልጆች ሥነ-ባሕሪ ላይ ተፅዕኖ ያሳድሩ ይሆን የሚለው ጥያቄ ተመራማሪዎቹን ጥናት እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል፡፡
ሕጻናት ቁሶቹን የንባብ ፣ የንግግር ፣ የተግባቦት እና የመሳሰሉትን የመስተጋብር ክኅሎቶች ለማዳበር ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡
አጥኚዎችን የሳበው ግን እንዴት እነዚህ ሰው ሰራሽ አስተውሎ የተካተተላቸው ቁሶቹ የልጆችን የአዕምሮ እና የማኅበራዊ ዕድገት በአሉታዊ መልኩ ይጎዱታል የሚለው ሃሳብ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ሕጻናቱ ከቁሶቹ ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር የቁሶቹ የተገደቡ ምላሾች በማኅበራዊ ዕድገታቸው ላይ ክፍተት በመፍጠር አዲስ ነገሮችን የመማር ክኅሎታቸው ሲጎዳ ተስተውሏል፡፡
ለአፕል “ሲሪ” ሕጻናቱ ምላሽ የሚሻ ጥያቄ በሚጠይቁበት እና ምላሽ በሚያገኙበት ጊዜ “እባክህ” እና “አመሠግናለሁ” የሚሉት ሐረጎች ማከል ግዴታ ባለመሆኑ እና ሐረጎቹን ልጆች አዘውትረው ባለመጠቀማቸው ወይም ግዴለሽነት በማሳየታቸው ቀስ በቀስ ከማኅበረሰባቸው ጋር የሚኖራቸው መሥተጋብር ጤናማ እንዳይሆን እንደሚያደርግ ጥናቱን የሰሩት ምሁራን አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ሕጻናቱ ለሚናገሩት ትህትና የተላበሱ ቃላት ከ“አሌክሳ”የሚሰጠውን አወንታዊ ማበረታቻ አጥኚዎቹ በበጎነት ተመልክተውታል፡፡
እነዚህ የሰው ሰራሽ አስተውሎ የግንኙነት መሳሪያዎች ለሕጻናቱ መረጃ ከመስጠት ባሻገር ሕጻናቱ ከኤሌክትሪክ ቁሶች ጋር በተያያዘ ለሚያነሱላቸው ጥያቄዎች በተግባር እንዲሞክሯቸው የሚያነሷቸው ምክረ-ሐሳቦችም ሰው ቢሆን የማይመክራቸው እና አደገኛ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ቁሶቹ የሰዎችን የግል የድምፅ ሚስጥሮች ቀድተው በማስቀረት ለሌሎች በኢሜይል ሲያካፍሉም ተስተውሏል፡፡
ይህም በግላዊነት እና ሚስጥራዊነት ላይ የዕምነት ጥያቄ ማስከተሉ ነው የተነገረው፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውሎ መሳሪያዎቹ መረጃ በፍጥነት በመሥጠት እና አዋቂዎች ላይ የሚታየውን ብቸኝነት በመቅረፍ ረገድ ያላቸው አበርክቶ በበጎነት ቢታይም ሕጻናትን ከዕውነታው ዓለም በመነጠልም ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረሱ መሆኑን አጥኚዎቹን ጠቅሶ ብሉምበርግ ቴክኖሎጂ አስነብቧል፡፡