አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 10 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አትሌት ብርሃኑ ፀጉ የተከለከለ የስፖርት አበረታች ቅመም መጠቀሙ በመረጋገጡ ለአራት ዓመታት በማንኛውም ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ እገዳ ተጥሎበታል።
አትሌት ብርሃኑ ባለፈው መስከረም ወር ዴንማርክ ኮፐንሀገን በተካሄደው የግማሽ ማራቶን የግል ውድድር ላይ የተከለከለ የስፖርት አበረታች ቅመም በመጠቀም ተጠርጥሮ ለሰባት ወራት ጉዳዩ ሲጣራ መቆየቱ ይታወሳል።
በተደረገው ተጨማሪ ማጣራትም አትሌቱ በግሉ በተሳተፈበት ውድድር ላይ በስፖርት የተከለከለ አበረታች መድኃኒት መጠቀሙ ተረጋግጧል።
አትሌቱ የፈፀመው ጥፋት የመጀመሪያው መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ከፈረንጆቹ መስከረም 15 ቀን 2019 ጀምሮ እስከ መስከረም 14 ቀን 2023 ድረስ ለአራት ዓመታት ከማንኛውም ሃገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ውድድር እንዳይሳተፍ እገዳ ተጥሎበታል።
ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ውድድር ላይ ያስመዘገበው ውጤት እና ሽልማት እንዲሰረዝ ውሳኔ መተላለፉን ከኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ አበረታች ቅመሞች ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision