አዲስ አበባ ፣ መስከረም 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስ እና ለመከላከል የሚያገለግለው የግብርና ኖራ ስርጭትን ተደራሽ ለማድረግ ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በግብርናው ዘርፍ የግል ሴክተሩን ያማከለ የግብርና ኖራ አቅርቦትና ስርጭት ሀገር አቀፍ የልምድ ልውውጥ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በግብርና ሚኒስቴር የግበዓት አቅርቦት ስራ አስፈጻሚ አቶ መንግስቱ ውብሸት እንደገለጹት፥ በሀገሪቱ እየታረሰ ካለው ጠቅላላ መሬት ውስጥ 41 በመቶ የሚሆነው በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ ነው።
በአሲዳማነት ከተጠቃው የእርሻ መሬት ውስጥ 28 በመቶ የሚሆነው የእርሻ ማሳ በከባድ አሲዳማነት መጠቃቱን ጠቅሰው÷ ችግሩን ለማቃለል የባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስ እና ለመከላከል የሚያገለግለው የግብርና ኖራ ስርጭትን ተደራሽ ለማድረግ ከግሉ ዘርፍ ጋር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
አርሶ አደሩ በኖራ አጠቃቀምና ውጤታማነት ላይ ያለውን ግንዛቤ ከማዳበር ጀምሮ የቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልሎችና የፌደራል ባለድርሽ አካላት በጋራ መስራት አለባቸውም ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት እየታረሰ ያለው 13 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት መሆኑን የገለፁት አቶ መንግስቱ ÷ የአፈር አሲዳማነት መጠኑ ከ5 ነጥብ 5 በመቶ በላይ በሆነ የእርሻ ማሳ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ምርትና ምርታማነትን እንደሚቀንስ ገልጸዋል።
በጂ አይ ዜድ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ፕሮጀክት የቴክኒክ አማካሪ አቶ ውብሸት ደምሴ በበኩላቸው ÷ በከፍተኛ አሲድ በተጠቃ የእርሻ ማሳ ምርትና ምርታማነት ከ50 እስከ 100 በመቶ እንደሚቀንስ ነው የገለጹት።
ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎና ባቄላ በአፈር አሲዳማነት በዋናነት የሚጠቁ የሰብል አይነቶቸ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ የእርሻ ማሳውን በግብርና ኖራ ማከም ከተቻለ እስከ 71 በመቶ የምርት ዕድገት ማግኘት ይቻላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።