አዲስ አበባ ፣ መስከረም 17 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መስቀል ከኃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር፣ የሀገራችን ስም በበጎ በማስጠራት፣ ባህላችን በማስተዋወቅና አንድነትን በማጠናከር ረገድ የበዛ ትሩፋት አለው ሲሉ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ገለጹ።
በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ እና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የመስቀል ደመራ በዓልን በደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን እና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በድምቀት አክብረዋል።
በደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በተደረገው ክብረ በዓል ላይ አምባሳደር ስለሺ በቀለ፥ የዋሺንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፋኑኤል እንዲሁም የእምነቱ ተከታዮች እና አባቶች ታድመዋል።
ብጹዕ አቡነ ፋኑኤል ባስተላለፉት መልዕክት የመስቀል በዓል የአንድነት እና የብርሃን ምልክት መሆኑን በመግለጽ ህዝበ-ክርስቲያኑም ይህን አብነት ይዞ ከመለያያት ይልቅ መተሳሰብን፣ ከአፍራሽነት ይልቅ ለሀገር ዘብ መሆን ማስቀደም አለበት ብለዋል።
ሀገራችንን አሁን የገጠሟትን ፈተናዎችን አልፋ ወደምትታወቅበት ሰላምና መረጋጋት እንድትመለስ አብሮነትን በማስረጽ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ እና የተጎዱ ወገኖችን ለማገዝ ቤቴክርስቲያኗ ምዕመኑን አስተባብራ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
አምባሳደር ስለሽ በቀለ በበኩላቸው “መስቀል ከኃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር፣ የሀገራችን ስም በበጎ በማስጠራት፣ ባህላችን በማስተዋወቅ እና አንድነትን በማጠናከር ረገድ የበዛ ትሩፋት ያለው፤ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚያከብሩት የአንድነትና የመተሳሰብ ምሳሌ እና በመላው ዓለም ደምቀን የምንታይበት ትልቅ በዓል ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
በሀገር ውስጥና በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንድ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው የሀገር ህልውናችን ለማጽናት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ሀገራችን በአሁኑ ወቅት በጽኑ የምትፈልገውን አንድነት፣ ተከባብሮ የመኖር እሴቶች፣ ድጋፍ የሚሹትን በመደገፍና የተጎዱትን በማጽናናት ቤተክርስቲያኗ የጀመረችውን አኩሪ ስራ አጠናክራ እንድትቀጥልም አምባሳደር ስለሽ ጥሪ አቅርበዋል።