የሀገር ውስጥ ዜና

አለመግባባትን በዕርቅ ዘግቶ በፍቅርና በሰላም ከመኖር የተሻለ ሌላ አማራጭ የለም-ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

By Feven Bishaw

September 26, 2022

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አለመግባባትን በዕርቅ ዘግቶ በፍቅርና በሰላም ከመኖር የተሻለ ሌላ አማራጭ የለም ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለጹ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ይህን የተናገሩት፥ የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት ሲከበር ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ነው፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው÷የምናከናውነው ተግባር በሙሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድና የመስቀሉን ምሥጢር የጠበቀ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ፍጥረታት በሙሉ እርስ በእርስ ሲጣሉና ሲተረማመሱ ማየት ቀዋሚ ትዕይንት ሆኖ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ምንም እንኳ ችግሩ በፍጥረታት ሁሉ ላይ ሰፍኖ ቢገኝም መፍትሔ የሌለው ችግር ግን አይደለም ነው ያሉት፡፡

በየጊዜው በተግባር የተፈተነ ጠንካራና የማያወላውል መፍትሔው ይቅርታና ዕርቅ ነው ያሉት ፓትርፓርኩ፥ ለሰው ልጅ አለመግባባትን በዕርቅ ዘግቶ ሰላምንና አንድነትን መሥርቶ በመከባበርና በመተሳሰብ፣ በመተዛዘንና በመተጋገዝ፣ በመረዳዳትና በመቻቻል፣ በፍቅርና በሰላም ከመኖር የተሻለ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ነው የገለጹት፡፡

ይህም እውን ሊሆን የሚችለው፥ ለወንድሜና ለእኅቴ የሚል ቅን አስተሳሰብ አንግቦ ለሁላችንም የሚል የጋራ አስተሳሰብ በሰዎች ልቡና የበላይነት ሲያገኝ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ፓትርያርኩ አክለውም፥ የመስቀልን በዓል በምናከብርበት በዚህ ቀን ከመስቀሉ መገኘት ባሻገር ማስታወስና ማሰብ ያለብን፥ የመስቀሉ ዓቢይ መልእክት በሰው ልጆች መካከል ፍጹም ሰላምና ፍቅር፣ አንድነትና እኩልነት፣ ይቅርታና ዕርቅ፣ ምሕረትና አዘኔታ በምልአት ሰፍኖ፣ የሰው መንፈሳዊ፣ ሞራላዊና አካላዊ ህላዌውና ጤንነቱ ያለምንም እንከን ተጠብቆ እንዲኖር ነው ብለዋል።

የምናከናውነው ተግባር በሙሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድና የመስቀሉን ምሥጢር የጠበቀ ሊሆን ይገባል ሲሉም ነው የገለጹት።

እግዚአብሔር ግጭቱን አስወግዶ ሰላሙን ፍቅሩን፣ አንድነቱንና ስምምነቱን እንዲያመጣልን፤ እኛም የዕርቅና የይቅርታ ሰዎች ሆነን እንገኝ ዘንድ በርትተን እንድንጸልይ አባታዊና መንፈሳዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን ብለዋል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፡፡

በመላኩ ገድፍ